የቻይና ኮሚዩኒስት ፓርቲ ድብቁ ታሪክ ክፍል ሁለት

Posted: November 28, 2012 in ሳይንሳዊ አምባገነንነትና ፍልስፍና


ግደይ ገብረኪዳን
ምንም እንኳ በአሁኑ ግዜ ስለ ቻይና ብዙ መልካም መገሮችን ብንሰማም፣ በአንድ ፓርቲ ጋርዮሻዊ አገዛዝ የምትተዳደር እንደመሆኗ ለማመን የሚከብዱ ክንውኖችም ይካሄዱባታል፡፡ በማኦ ዘመን የባህል አብዮት በታወጀበት ግዜ ከነበረው ጭቆና አሁን ቢሻልም አሁንም ቢሆን ቻይና ከባድ ሃገር ነች፡፡ የፓርቲው አባላት የግዴታ ኢ-አማንያን መሆን ይጠበቅባቸዋል፣ ተቃዋሚሆች ያለህግ አግባብ እርምጃ ይወሰድባቸዋል፣ ቲቤት ፈተና ውስጥ ነች፣ ፓርቲው አስገዳጅ ፖሊሲዎችን ያወጣል ለምሳሌ አንድ ልጅ ብቻ የመውለድ ፖሊሲ የቻይና ወላጆችን እያሰቃየ ነው – በቻይና ወንድ መውለድ ስለሚፈለግ ተፈጥሯዊ ባልሆነ መልኩ የወንዶች ቁጥር ከሴቶች እንዲበልጥ አድርጓል፣ ሴት ስትፀነስ ውርጃ ይካሄዳል – ተወልደውም የሚገደሉ አሉ፡፡ መንግስት በቀጥታ ሚድያውን ሁሉ ይቆጣጠራል፣ መንግስትን የሚወቅሱ ፅሁፎች የማይታሰብ ነው፣ በኢንተርኔት የሚወጡትም ከሰው እንዳይደርሱ ይታገዳሉ፡፡

ከሁሉ የከፋው ክርስትያኖች ላይ የሚደርሰው ጭቆና ነው፡፡ ካቶሊኮቹ ለቻይና አርበኛ ካቶሊኮች ማህበር ተጠያቂ ሲሆኑ ሌሎቹ ደግሞ በሌላ ቁጥጥር ይደረግባቸዋል፡፡

ጃፓን እና ማንቹርያ

ዛሬ ቻይናን እየገዛ ያለው መንግስት በአሜሪካ መንበረ ስልጣኑ የተሰጠው ነው፡፡ ይህ ለብዙ ሰዎች ማመን የሚከብድ ነው፡፡ በ1930 ዎቹ ጃፓን በወታደራዊ ጡንቻዋ ፈርጣማ እያለች ሶቭየት ህብረት ኤስያን ጋርዮሻዊ ለማድረግ ለነበራት እቅድ እንቅፋት ትሆንባት ነበር፡፡ የዩ.ኤስ. ኮሚኒስት ፓርቲ መስራች አባል የሆነው ቤንጃሚን ጊትሎው አይ ኮንፌስ (1940) በሚለው መፅሃፉ ራሽያ በነበረበት ወቅት ራሽያውያኑ በሳይቤርያ ድንበራቸው በኩል የነበራቸውን ስጋትና በኤስያ የመስፋፋት እቅዳቸውን አሜሪካ ጃፓንን አስወግዳላቸው በአሜሪካውያኑ ደም ህልማቸውን እውን የማድረግ ምኞት እንደነበራቸው ፅፏል፡፡ (እውንም ሁኗል፡፡)
በ1935 በሞስኮ የዩ.ኤስ አምባሳደር የነበረው ዊልያም ሲ. ቡሊት ወደ ዋሽንግተን የውጭ ጉዳይ ቢሮ ሃላፊ ኮርዴል ሁል የተወካዮች ቡድን ልኮ ነበር፡፡ በዚህም የሚከተለውን ማስጠንቀቅያ ልኳል፡ ሶቭየቶች አሜሪካ ከጃፓን ጋር ጦርነት ውስጥ እንድትገባ ከልባቸው የሚመኙት ሲሆን ከዚህም ሶቭየቶች ክስተቱን ማንቹርያን ለመቆጣጠርና ቻይናን ሲቭየታዊ ለማድረግ እንደሚጠቀሙበት አሳስቦ ነበር፡፡
በ1930ዎቹ ነበር ጃፓን ሰራዊቶቿን ወደ ማንቹርያ (ሰሜናዊ ቻይና) ያስገባችው፡፡ መማርያ መፃህፍት ይህን የመስፋፋት (ኢምፐርያሊስት) ወረራ ይሉታል፡፡ ሆኖም ግን ይህ የጃፓን እርምጃ ከብሄራዊ ደህንነት አንፃር የተተገበረ ነበር፡፡ ሶቭየቶች ሲንክያግን እና ሞንጎልያን በመቆጣጠራቸው የሰጠችው የጥንቃቄ እርምጃ ነበር፡፡ እንዲህ ባታደርግ ኑሮ ጋርዮሻዊነት በመላው ኤስያ ተስፋፍቶ ለራሷም ስጋት ይሆናት ነበር፡፡

የቻይና ሪፐብሊክ

ቻይና የኩዊንግ ስርወመንግስት እስኪወገድ ድረስ እስከ 1911 ድረስ በነገስታት ነበር የምትተዳደረው፡፡
አብዮቱን ያካሄደው ሰን ያት ሰን ነበር ቻይናን ህገ መንግስታዊ ሪፐብሊክ ለማድረግ ነበር፣ በኮሚንታንግ ወይም የቻይና ብሄራዊ ፓርቲ እየተመራ፡፡ በዚህ መልካ ሃሳብ ግን ሰፊውን ቻይና ማዋሃድ ከባድ ስራ ነበር፡፡ ንጉሱ ከወደቀ በኋላ ቻይና በከባብያዊ መሳፍንት ነበር የምትገዛው፣ በ1925 ሰን ከሞተ በኋላ ቻይናን በዚህ መልካ መሰረት የማዋሃድ ሃላፊነቱ ሻንግ ካይሼክ ላይ ወደቀ፣ ሻንግ ካይሼክ ክርስትያን እና የኮሚንታግ መሪ ነበር፡፡
ኮሚንታንግን ሶቭየቶች ሰርጎ ለመግባት ያደረጉት ጥረት ሻንግ ካይሼክ ቀድሞ በማየቱ በ1928 የሶቭየት ወኪሎችን በማባረር አክሽፎታል፡፡ በዚሁ ዓመት በ1928 ፎረይን አፈየር የተባለው የሴረኛው የሲ.ኤፍ.አር. (ወይም የውጭ ጉዳየች መማክርት) ሻንግ ካይሼክን በመውቀስ ፅሁፍ አመጣ፡፡ ሲ.ኤፍ.አር. ማለት ከአንደኛ ዓለም ጦርነት በኋላ በቁንጮዎቹ የተመሰረተ ተቋም ሲሆን የሲ.ኤፍ.አር. አባሎች የአሜሪካ ፖለቲካ በቁጥጥራቸው ስር ነው፡፡(ዲሞክራትም ሆነ ሪፐብሊካን እራሱ እና አማካሪዎቹ ሁሉ ከዚሁ ተቋም አባል የሆኑ ናቸው፡፡)
ከዚህ እለት ጀምሮ ሻንግ ካይሼክ የሶቭየት ህብረት እና የአሜሪካ ቁንጮዎች ተቋማት ፀበኛ ሆነ፡፡

ቀዮቹ ቻይኖች፡ የሶቭየት አሻንጉሊቶች

የቻይና ኮሚውኒስት ፓርቲ የሶቭየት ህብረት አሻንጉሊት ነበር፡፡ ቻይና ላላት እጅግ ሰፊ የሰው ሃብት መጪው እጣው በጋርየሻዊነት መስራት እንደሆነ ተቀብለዋል፡፡ በ1933 የቻይና ኮሚውኒስት ፓርቲ ለሶቭየት አምባገነኑ ጆሴፍ ስታሊን የሚከተለውን ደብዳቤ ፅፈው ነበር፡ “ከድል ወደ ድል ምራን፣ ኦ የኛ መሪ (ፓይለት)!”
ስታሊን የሻንግ ካይሼክ ብሄራዊ መንግስት እንዲገለበጥ ብዙ ይሰራ ነበር፡፡ በ1937 ጃፓን ወደ ማንቹርያ ስትገባ ግዜ ሻንግ ካይሼክ ይመክታቸው ስለነበር ስታሊን ኮሚውኒስቶቹ ሻንግ ካይሼክ ላይ ያደርሱ የነበረውን ጥቃት እንዲቀንሱ አዟቸው ነበር፡፡ ይህም ጃፓን በኤስያ ለነበረው እቅዱ ፀር ስለሆነች ነበር፡፡
አሁን አሜሪካ ሻንግ ካይሼክን የማገዝ ግዴታ ሊኖርባት ነው፡፡ ቻይና ኮሚውኒስቶች መሪ ማኦ ዚዶንግ የሚከተለውን ብሎ ነበር፡ “ፖሊሲያችን 70 መቶኛ እራሳችንን ማሳደግ፣ 20 መቶኛ ተስማምተን ማለፍ (ኮምፕሮማይዝ ማድረግ)፣ 10 መቶኛ ደሞ ጃፓኖችን መዋጋት ነው፡፡” ብሎ ነበር፡፡ ቀዮቹ ጃፓን ላይ እጅግ ዝቅተኛ ጉልበት ነበር የመደቡት፣ በብዛት ሊጥሉት ሲሞክሩ የነበረውን የብሄራዊውን መንግስት መውጋት ላይ ነበር ያዋሉት፡፡ ሮበርት ዌልች የቻይናን አወዳደቅ በዳሰሰበት Again, May God Forgive Us የተሰኘው መፅሃፉ የሚከተለውን ዘግቦ ነበር፡ “አንድ ምሳሌ ለመጥቀስ በ1943 በሻንቱንግ እነሱ (ኮሚውኒስቶቹ) በደቡብ በኩል ወደ ሃያ ሺህ የሚጠጋው የብሔራዊ ጦሩን ሲያጠቁ በተመሳሳይ በዚሁ ግዜ በሰሜን በኩል ደግሞ የጃፓን ሰራዊት ሲያጠቃቸው ነበር…” ብሏል፡፡

የሮዘቬልት ክህደት

የቻይና ውድቀት የመጣው ግን በኮሚውኒስቶቹ ጥቃት ብቻ አልነበረም፡፡ በ1943 በቴህራን ኮንፍረንስ እና በ1945 በያልታ ኮንፍረንስ ሮዘቬልት ከስታሊን ጋር ከተነጋገረ በኋላ የመጡ ውሳኔዎች ነበሩ፡፡ ስታሊን ጀርመንን በመፃረር የአሜሪካ ወዳጅነት ስምምነት ቢኖረውም፣ ከጃፓን ጋር ግን ጦርነት ውስጥ ያለመግባት የሁለትዮሽ ስምምነት ነበረው፡፡ ይህ ለስታሊን ተመችቶት ነበር ምክንያቱም ጃፓኖች የቻይና የብሄራውያን ሃይሎችን ስለሚያዳክሙለት ነው፡፡
በቴህራን እና ያለታ ስምምነቶች ግን ሮዘቬልት ስታሊን ከጃፓኖች ጋር ያለውን ስምምነት እንዲሰርዝ ጠይቀውታል፡፡ ስታሊን ቢቀበልም ቅድመ ሁኔታዎችን ግን አስቀምጦ ነበር፡፡ በሩቅ ምስራቅ ለሚያደርገው ዘመች ሙሉ ትጥቁን አሜሪካ እንድትሸፍን ማለትም፡- 3000 ታንኮች፣ 5000 አውሮፕላኖች፣ እና ሌላ አስፈላጊ ትጥቅ በሙሉ፣ እና ለ1,250,000 ጦር ሰራዊት ከሚያስፈልገው ስንቅ፣ ነዳጅ ሁሉ እንድታሟላ፡፡ ሮዘቬልት ይህን ተቀብሎ በሌንድ-ሊዝ መርኃ ግብር መሰረት 600 መርከብ ጭነት አሜሪካ ለሶቭየቶች አቅርባለች፡፡ የስታሊን የሩቅ ምስራቅ ሰራዊት ብቻ ሻንግ ካይሼክ የአራት አመት የትግል አጋ ሁኖ ካገኘው በሁለት እጥፍ የሚበልጥ ድጋፍ ተደረገለት፡፡ ጀነራል ዳግላስ ማካርቱር ለፓሲፊክ ሰራዊቶቹ አቅርቦት ሲጠብቅ የነበረው ወደ ሶቭየቶች መቀየሱን ሲደርስበት ተቃውሞውን አሰምቷል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ በቻይና የበላይነትን የሚያስገኙ ሁለት ስትራቴጅያዊ ወደቦችን ደይረን እና ፖርት አርቱር ሮዘቬልት የቻይና አጋሮቹንም ሆነ የአሜሪካ ምክር ቤትን ሳያማክር በስታሊን እጅ እንዲሆኑ ስምምነት ፈፅሟል፡፡ የዚህ ሁሉ ሶቭየቶችን የማስታጠቅና ቁልፍ ቦታዎችን የማስያዙ ጉዳይ ለጦርነቱ ተብሎ ሳይሆን ሶቭየቶችን ለማፈርጠም ተብሎ የተደረገ ነበር፡፡ ስምምነቱን ያረቀቀው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ቢሮ ተወካይዋ አልገር ሂስ የሚባል ነበር – ይህ ሰው ግዜውን ጠብቆ የሶቭየቶች ሰላይ እንደሆነ የተጋለጠበት በአሜሪካ ፖለቲካ ታሪክ አስገራሚው ቅሌት የተፃፈለት ሰው ነው፡፡ በቻይና የአሜሪካ አምባሳደር የነበረው ጀነራል ፓትሪክ ኸርሊ፡ “በሚስጥራዊው የያልታ ስምምነት የአሜሪካ ዲፕሎማቶች የቻይና ዳር ድንበር እና ፖለቲካዊ ነፃነትን አሳላፈው ሰጥተዋል … በኮሚኒስት እንድትያዝም መንገድን ጠርገዋል፡፡” ሲል ፅፏል፡፡
ሩቅ ምስራቅን እንዲወር ስታሊንን የማስታጠቅ ውሳኔ በአሜሪካ ዲፕሎማሲያዊ ታሪክ ትልቁ ቅሌት ነበር፡፡ የስታሊን ጦር ሰራዊት የተሸነፈውን የጃፓን ሰራዊት ሊዋጋ በ9 ኦገስት፣ 1945 ወደ ቻይና ዘመተ፡፡ በዚህን ግዜ የአቶም ቦምቡ ሂሮሺማ ላይ ቀድሞ ተጥሎ ነበር፡፡
ገና ብዙም ተኮሱ ሳይባል ሶቭየቶች ማንቹርያ የነበረውን እጅግ ብዛት የነበረውን የጃፓንን ትጥቅ ተረከቡ፡፡ ይህንና በሌንድ-ሊዝ መርሃ ግብር ከአሜሪካ የተረከቡትን መሳርያ ለማኦ ዚዶን ሰራዊት አስታጠቁ፣ በአሜሪካ መስራች አባቶች መርህ መሰረት ሪፐብሊካዊ ብሔራዊ መንግስት የመሰረተው ክርስትያኑ ሻንግ ካይሼክ መንግስትን እንዲገለብጡበት፡፡

ኮምጣጣ ጆ

ሌላ ብሔራውያኑን ለማጥፋት የተከተሉት ስልት፡ ከዩ.ኤስ ለቻይና የተመደቡተ ሰዎች ነበሩ፡፡ ከሁሉም የባሰው ጀነራል “ኮምጣጣ ጆ” ስቲልዌል ነበር፡፡ በጦር ስትራቴጂ አውጪነቱ አድናቆት ቢያገኝም ለሻንግ ካይሼክ የነበረው ጥላቻ ግን የሚታወቅበት ነገር ነበር፡፡ ቅፅል ስም አውጥቶ “ለውዝ” እያለ ይጠራው ነበር፡፡ በተጨማሪም ለኮሚውኒስቶቹ ያለው አድናቆትም ድብቅ አልነበረም፡፡ ስቲልዌል አንዴ፡ “አካፋዬን ጥዬ ከቹ ቴ ጋር ጠመንጃ ብሸከም ደስ ይለኝ ነበር፡፡” ሲል ፅፎ ነበር፡፡ ቹ ቴ ማለት የኮሚውኒስቶቹ ሰራዊት ዋና መሪ ሲሆን በኋላ ላይ በኮርያ ጦርነት ግዜ የአሜሪካ ሰራዊቶችን ሲገድል ነበር፡፡
ጃፓኖች የቻይናን ወደቦች ተቆጣጥረው ስለነበር የቻይናው ብሔራዊ መንግስት ትጥቅ በአየር በህንድ በኩል ነበር የሚደርስለት፡፡ ስቲልዌል በምድር በኩል በር ለመክፈት በበርማ መስመር ጃፓኖችን ሲዋጉ ስቲልዌል አመራር ሲሰጥ ነበር፡፡ ዘመቻው ሲከሽፍ ስቲልዌል 30 የብሔራውያኑ  ክፍለ ጦሮችን ይዘን ደግመን ካሞከርን ብሎ ሞግቷል፡፡ ሻንግ ካይሼክ ይህን ተቃወመ፣ ምክንያቲም 30 ያክል ክፍለ ጦር ወደ ደቡብ መላክ ክፍተት ስለሚፈጥር ለኮሚውኒስቶቹ እና ለጃፓኖች ሌላ በር ይከፍትላቸዋል በሚል ነበር፡፡ የዝነኞቹ “በራሪዎቹ ነብሮች” የሚባሉት ሰራዊቶች መሪ የነበረው ጀነራል ክሌር ቼናውት ከሻንግ ጋር በሃሳቡ ትክክለኛት ተስማማ፡፡ ስቲልዌል በዚህ አጋጣሚ የሚያደንቃቸው ኮሚውኒስቶች ሰራዊትን ለመጠቀም ተጨማሪ ሃሳብ አልሰጠም፡፡
ስቲልዌል ብስጭቱን ለፕሬዚደንት ሮዘቬልት በሚናገርበት ወቅት ሮዘቬልት ሻንግ ስቲልዌልን የመላ ቻይና ብሄራውያን ሃይሎች “ገደብ የለሽ አዛዥ” እንዲያደርገው እና ሰራዊቶቹንም ወደ በርማ እንዲልክ ትእዛዝ ሰጠው፡፡ ይህን የትእዛዝ መልእክት ስቲልዌል ለሻንግ ከሰጠ በኋላ በማስታወሻ ደብተሩ የሚከተለውን አስፍሯል፡
ለመበቀል ለረዥም ግዜ ስጠብቅ ነበር – በመጨረሻ እድሉን አግኝቻለው፡፡ ለውዙን ዓይኑን እያየሁ በካልቾ አልኩት፡፡ … ይሄ ደቃቃ ዲቃላ እየተንቀጠቀጠ መናገር አቃተው፡፡ ፊቱ አረንጓዴ ሆነ፣ እየተንቀጠቀጠ ላለመጮህ ሲታገል ነበር፡፡
የስቲልዌል እቅድ ግን አልተሳካም፡፡ ሻንግ የሮዘቬልትን ትእዛዝ አልቀበል፣ም በማት ስቲልዌልን በሌላ ሰው እንዲቀይር ጠየቀ፡፡ እንዲህ ካሆነ ግን ጃፓኖችን ለብቻው እንደሚዋጋ አሳወቀ፡፡ ልክ ከፐርል ሃርበር ድብደባ ከአራ አመት በፊት ጀምሮ ሲያደርግ እንደነበረው ማለት ነው፡፡ ሮዘቬልት ሳይወድ ተስማማ፡፡ ይባስ ብሎ ስቲልዌል እንዲበሽቅ የተካው ጀነራልአልበርት ሲ. ዌድመየር ከሻንግ ጋር አንድ ዓይነት አመለካከት ያላቸው ሆኑ፡፡ 
ሻንግ ካይሼክ የሚከተለውን ፅፎ ነበር፡ “ ስቲልዌል ከኮሚውኒስቶቹ ጋር ሁኖ መንግስት ለመገልበጥ ሲያሴር ነበር፡፡” ይህ አምባሳደሩ ጀነራል ኸርሌ የሚስማማበት ነው፡ ጀነራል ስቲልዌል ማህደር በቻይና የቻይና ብሔራዊ መንግስትን የመፈንቀል እና በኮሚኒስታዊ መንግስት የመተካት ማህደር ነው – እና ይህ ሁሉ እንቅስቃሴ ደሞ በወቅቱ በዋሽንግተን አስተዳደር (መንግስት) ውስጥ ከነበረው የኮሚኒስት ህዋስ አካል ነው፡፡” ሲል በቻይና የአሜሪካ አምባሳደር የነበረው ጀነራል ኸርሌ ፅፏል፡፡

የውጭ ጉዳይ ቢሮው ቡድን

አምባሳደር ኸርሌ ስለምን “ህዋስ” ነው እያወራ ያለው? ቻይና እያለ በቢሮው ሃገሪቱ በኮሚኒስቶች እጅ እንድትገባ በሚሰሩ ሰዎች ተከቦ ነበር፡፡ ዲን ኤክሰን ወጣት እያለ በአሜሪካ የሶቭየት ጉዳይ አስፈፃሚ ሁኖ ይሰራ የነበር ጠበቃ ነበር፣ በ1941 በውጭ ጉዳይ ቢሮ ረዳት ዋና ፀሃፊ (ምክትል ሚኒስቴር) ሆነ፡፡ በዚህ ስልኑም ተጠቅሞ የሩቅ ምስራቅ ዲፕሎማቶች በጠቅላላ ኮሚኒስቶች እና ኮሚኒስት ደጋፊዎች፣ የተጋለጠው አልገር ሂስን ጨምሮ እንዲሆኑ አድርጓል፣ በተጨማሪም ጆን ካርተር ቪንሰንት የሩቅ ምስራቅ ጉዳየች ቢሮ ዳይሬክተር በኋላ በደይሊ ዎርከር አምደኛ ለዊስ በደንዝ (Louis Budenz) ኮሚኒስት መሆኑን ያጋለጠው፣ የውጭ ጉዳይ ሚስጥሮችን ለቻይና ኮሚኒስቶች ሲያቀብል የነበረው ጆን ስቴዋርት ሰርቪስ በቻይና የውጭ ጉዳየች አገልግሎት ኦፊሰር (ይህ ሰው በኤፍ.ቢ.አይ. በአመርኤዥያ የስለላ ክስ ተይዞ የታሰረ ነው፣ ለኮሚኒስቶቹ በሎቢነት ጉዳይ ሲያስፈፅም የነበረው የውጭ አገልግሎት ኦፊሰሩ ጆን ፒ. ዴቪስ፣ ኦውን ሊትሞር በዩ.ኤስ. ለሻንግ ካይሼክ አማካሪ እንዲሆን የተሸመው እና በኋላ ላይ ከቅዠታቸው የነቁት ኮሚኒስትነታቸውን የተውት ዋይታከር ቻምበርስ እና ኤልሳቤት ቤንትሊ ኮሚኒስት እንደሆነ ያጋለጡት፣ እና ሌሎችም ይገኙበታል፡፡
በንዴዝ እንደፃፈው፡ “ኮሚኒስቶቹ በልኡካኑ እና በጆን ካርተር ቪንሰንት ላይ ተመስርተው ነበር አምባሳደር ኸርሊ ላይ ዘመቻቸውን የከፈቱት፡፡”  ሀቀኛ ባለስልን የሆነው ኸርሊ ከስሩ ባሉ ሰዎች ሴራ እጅግ ተገርሞ ነበር፡፡ ለትሩማን በላከው ሪፖርትም፡ “የውጭ ጉዳይ አገልግሎ ልኡካኑ ከታጠቀው የኮሚኒስት ፓርቲ ጋር ነው የወገኑት፡፡” ሲል ፅፏል፡፡
ኸርሊ በስሩ ካሉት የውጭ ጉዳይ ቢሮ ሰራተኞች 11 ሰዎችን አባሯል፡፡ እኚህ ሰዎች ተባረው ከቻይና ወደ አሜሪካ ከተመለሱ በኋላ በሚደንቅ መልኩ እድገት ተሰቷቸው አንዳንዶቹ ከኸርሊ በላይም ሁነዋል፡፡ ከዚህ በኋላ ኸርሊ ስራውን በፈቃዱ ለቋል፡፡ “እኚህ ፕሮፌሽናል ዲፕሎማቶች ወደ ዋሽንግተን ተመልሰው በሩቅ ምስራቅ እና ቻይና ጉዳዮች ክፍል የኔ የበላዮች ሁነው ተሸመዋል፡፡” ሲል ፅፏል፡፡

ኮሚኒስት የሚጠቅሙ ስትራቴጂዎች

ይህ የውጭ ጉዳይ ህዋስ የቻይና ኮሚኒስቶችን ለመጥቀም የተለያዩ ስትራቴጂዎችን ይከተል ነበር፡፡ ከዚህም ዋናው አንዱ የማኦ ተከታዮች ኮሚኒስቶች አይደሉም ለውጥ የፈለጉ ገበሬዎች ናቸው እያሉ ማስተባበል ነበር፡፡ የካርል ማርክስ ኮሚኒስት ማኒፌስቶ “የዓለም ላብ አደሮች ተባበሩ!” ቢሆንም መፈክሩ በቻይና ብዙ ኢንዱስትሪ ስላልነበር የቻይና ኮሚኒስቶች ፊታቸውን ወደ ገበሬዎቹ ሊያዞሩ ችለዋለዋል፡፡ ኮሚኒስት እንዳልሆኑ የፃፉትን እና የተናገሩትን እዚህ ማጣቀስ አያስፈልግም፡፡ የሌባ ዓይነ ደረቅ … እንደሚሉት አሁን ደሞ ሌላ ምክንያት መጨመራቸው የማይቀር ነው፡፡
ከውጭ ጉዳይ ቢሮ የሆነው ጆን ፒ. ዴቪስ ለዋሽንግተን ሪፖርት ሲያደርግ፡ “ቻይና የኮሚኒስቶቹ ነች፣ የቻይና እጣ ፈንታም ከኮሚኒስቶቹ ጋር ነው እንጂ ከሻንግ ካይሼክ ጋር አይደለም፡፡” ተጨማሪው ዘዴ እንግዲህ የተከተሉት ሻንግ ካይሼክን እና ብሔራውያኑን እንደ “ፋሺስት”፣ “አድሃርያን” እና “ብልሹ” እድርጎ ማቅረቡ ነበር፡፡  ጀነራል ዌድመየር እውነታውን እንደሚከተለው ያሳየናል፡
“ምንም እንኳ ብሔራዊው መንግስት በተደጋጋሚ እና ጥላቻ በተሞላበት ሁኔታ እንደ አምባገነን ተደርጎ ቢነገርም በነሱ እና በኮሚኒስት ጠላቱ መሃከል ያለው ልዩነት የኮሚንታንጉ (የብሔራውያኑ) የመጨረሻ ግብ ህገ መንግስታዊ ሪፐብሊክ መመስረት ሲሆን የኮሚኒስቶቹ ግን በሲቭየት መስመር ተከትለው ሁሉን አቀፍ አምባገነናዊ መንግስት መመስረት መሆኑ ላይ ነው፡፡ ከሻንግ ካይሼክ ጋር በነበረኝ የሁነት ዓመት ቅርብ ግንኙነት ምክንያት በግሌ ሻንግ ካይሼክ ቀጥተኛ፣ እራሱን የማይወድ፣ ለህዝቡ ደህንነት የሚያስብ እና ህገ መንግስታዊ መንግስት የመመስረት ፍላጎት ያለው መሆኑን አምናለው፡፡”
ብልሹነት ወይም ሙስና በሁሉም መንግስታት ያለ መሆኑን ዌድመየር በማስተዋል ሳይገልፅ አላለፈም በዋሽንግተንም ሳይቀር፡፡ በቻይና ግን የአሜሪካ ሴራ ሲታከልበት ችግሩን ያባብሰዋል፡፡ በጃፓን በደረሰባቸው ውድመት ብሄራውያኑ በወረቀት ገንዘብ (አሁን ዓለም ላይ እንዳለው ማለትም ዋስትና የሌለው መገባያያ) እንዲጠቀሙ አስገድዷቸው ነበር፣ በዚህም የተነሳ ቻይና ከባድ የዋጋ ግሽፈት ውስጥ ገባች፡፡ ሁኔታውን ለማረጋጋት ሻንግ ከአሜሪካ የወርቅ ብድር ጠይቋል፡፡ ፕሬዚደንት ሮዘቬልት ጥያቄውን ቢያፀድቅም የግምጃ ቤት ዋና ፀሃፊው (ገንዘብ ሚኒስትሩ) ሃሪ ዴክስተር ዋይት ወርቁ እንዳይጓዝ የማስተጓጎል ስራ ሰርቷል፡፡ ሃሪ ዴክስተር ዋይት በኋላ ላይ የሶቭየት ሰላይ መሆኑ የተጋለጠበት ሌላው ቅሌታም እጅግ ከፍተኛ የአሜሪካ ባለስልጣን ነው፡፡ ይህ የቻይናን መገበያያ እንዲከስም አድርጎታ፡፡ ከዚህም የተነሳ ባለስልጣናቱ እንዴት ፊታው ወደ ሙስና ሊዞር እንደቻለ መረዳ ይቻላል፡፡
ዋልር ኤስ. ሮበርት በውጭ ጉዳይ የሩቅ ምስራቅ ጉዳዮች ረዳት ዋና ፀሃፊ ለናሽናል ፕሬስ ክለብ በ1959 እንዲህሲል ተናግሮ ነበር፡ “ቻይና ወደ ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ስትገባ ፀጥ ብለን ቁመን ስናይ ነበር፡፡ … በኔ አመለካከት ሁኔታውን ማዳን በምንችልበት ብቸኛ ግዜ ላይ ፈንድ ሳንለቅ ቀርተናል፡፡ ምን ለማድረግ ነው? ኮሚኒስቶች በሃይል ለማስገባት፡፡”
በመጨረሻ ስትራቴጂያቸው ውጭ ጉዳይ የነበሩት ግራ ዘመሞች ብሔራዊው መንግስት ከኮሚኒስቶቹ ጋር ጥምር መንግስት እንዲመሰርት መወትወት ጀመሩ፡፡ ይህ ያረጀ ኮሚኒስት ስልት ነው፡፡ ጦርነቱ ካለቀ በኋላ በፖላንድ፣ ዩጎዝላቭያ እና ቼኮዝለቫግያ ያሉት መንግስታት ከኮሚኒስቶቹ ጋር ጥምር መንግስት እንዲመሰርቱ በማስገደድ፣ ከግዜ በኋላ ሁሉ በኮሚኒስቶቹ ቁጥጥር ስር ሆነ፡፡ ማኦ ዚዶንግም ለቻይና እንዲሁ ዓይነት ዘዴ ይታየው ነበር፡፡ ለሰባተኛ የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ ጉባኤ በጥምር መንግስት ዙርያ ባቀረበው ሪፖርቱ ማኦ ጥምረት ሁለቱንም ሻንግን እና አድሃሪው የአሜሪካ ኢምፐርያሊዝምን እንደሚያጠፋላቸው ፅሁፉን አቅርቦ ነበር፡፡
ቻይና ውስጥ የነበረው የውጭ ጉዳይ ቡድን ይህን የማኦ ጥሪን በጆን ፒ. ዴቪስ በኩል እንደ ብቸኛ መፍትሄ ተደርጎ እንዲቀርብ ሲያደርጉ ነበር፡፡ ሁለቱን ህገ መንግስታዊ ነፃነትን እና አምባገነናዊ ማን አለብኝነትን ለማዋሃድ የሚደረገው ሙከራ በዳግላስ ማካርቱር ውሃ እና ዘይትን ማዋሃድ የመሞከር ያህል ነው ሲል ያነፃፅረው ነበር፡፡
እንድያውም በሚገርም ሁኔታ ሻንግ ካይሼክ ከጦርነቱ በኋላ ሁሉን ቻይና የሚወክል መንግስት ለመመስረት እቅድ ነበረው፡፡ በህዳር 1946 ለ 40 ቀናት ውይይጥ ያደረገ ከመላው ቻይና የመጡ 2,045 ተወካዮችን የያዘ ብሔራዊ ጉባኤ አካሂዶ ነበር፣ በዚህም የሃገሪቱን ህገ መንግስት አፅድቀዋል፡፡ ምንም እንኳ ጥምር መንግስት እያሉ ቢንጫጩም የማኦ ኮሚኒስቶች ከመሳተፍ እራሳቸውን አግደዋል፣ በቻይና የብዙሃኑ ድጋፍ ስለሌላቸው ስልጣን በሃይል ብቻ እንደሚያገኙት ስለገባቸው ነበር፡፡


የማርሻል ልኡካን

ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወደመገባደዱ ሲቃረብ የማኦ ሰራዊቶች በራሽያ አስታጣቂነት – አሜሪካ በሌንድ0ሊዝ የሰጠቻቸውንና ከጃፓኖቹ የተረከቡትን ተጠቅመው ያስታጠቋቸውን ማለት ነው – ሙሉ ጥቃታቸውን በብሔራዊው መንግስት ላይ ጀመሩ፡፡ የማኦ አማፅያን ጆርጅ ማርሻል ጣልቃ ባይገባላቸው ኑሮ ሽንፈትን ይቀምሷት ነበር፣ ማርሻል ፕሬዚደንት ትሩማ የመደበው በቻይና ልዩ የአሜሪካ ተወካይ ነው፡፡
ማርሻል ሁሌም ቢሆን “ትክክል ባሆነ ቦታ እና ግዜ” የመገኘት እጣፈንታ ነበረው፡፡ ፕሬዚደንት ሮዘቬልት ያለአግባብ ስንት የበላዮቹን ትተው ያለ ቅጥ በመሾም እላይ የሰቀሉት ሰው ነው፡፡ የዩ.ኤስ. ሰራዊት ዋና አዛዥ በማድረግ፡፡ በዛ ቦታ ላይ ሁኖ በታህሳስ 7፣ 1941 እየመጣ ስላለው ስለ ፐርል ሃበር ጥቃት ሊያሳውቁት ኦፊሰሮቹ ሲፈልጉት ፈረስ ሊጋብ ሂዶ ከቢሮው ሊያገኙት አልቻሉም ነበር፡፡ (ጥቃቱ ቀድሞውኑ የታወቀና አሜሪካን ወደ ጦርነቱ ሆን ብለው እንዲሆን የፈቀዱት ነው፡፡) በኮርያ ጦርነት ግዜ ደሞ መከላከያ ዋና ፀሃፊ (ሚኒስቴር) ተደረገ፣ በዚህም ስልጣኑ ስትራቴጂካዊ ጥቅም የነበረውን የያሉ ድልድይ ጀነራ ማካርቱን እንዳያፈርሰው በማዘዝ ሲረብሽ ነበር፣ በዚህም ኮሚኒስት ቻይና ሰራዊት ድልድዩን እንደ ልባቸው ሲጠቀሙበት ነበር፡፡ የትም ቦታ ቢቀመጥ ማርሻል ባለበት ሁሉ አሜሪካ ስትወድቅና ኮሚኒዝም ሲለመልም ነበር፡፡ ይህ ሁኔታ ስሙ ያለ አግባብ እንዲጠፋ ያደረጉት ሴናተር ጆሴፍ ማካርቲ America’s Retreat from Victory: The Story of George Catlett Marshall መፅሃፉ የሰውየውን ስራ ዘግቦታ፡፡
ወደ ቻይና ከመንቀሳቀሱ በፊት የኮሚኒስቶቹን ፕሮፖጋንዳ እንደተቀበለ ታውቆበት ነበር፡፡ ባለ አምስት ኮከቡ የባህር ሃይሉ አድማይራል ዊልያም ሌሂ (Admiral William Leahy) እንደተናገረው፡ “ማርሻል ወደ ቻይና ሲሄድ ነበርኩኝ፡፡ እሱም [ማርሻልም] ለሻንግ ከኮሚኒስቶቹ ጋር እንዲስማማ አልያም ያለ እኛ ድጋፍ መኖር እንደሚችል እነግረዋለው ሲል ነበር፡፡ ከተመለሰ በኋላም ይህኑኑ ሲናገር ነበር፡፡” ማኦ ዚዶንግ እና ተከታዮቹ ኮሚኒስቶች እንደሆኑ ሲነገረው “ሞኝ አትሁኑ እኚህ ሰዎች የጥንቱ ለውጥ ፈላጊ ገበሬዎች ናቸው፡፡” ይል ነበር፡፡
ማርሻል መጀመርያ ቻይና ሲሄድ ብሔራውያኑ ኮሚኒስቶቹን በቁጥር 5-1 ይበልጧቸው ነበር፣ በሰራዊትም በትጥቅም፣ በተሳካ ሁኔታም እያሸነፏቸው ነበር፡፡ ማርሻል እንደሄደ ሶስት የሰላ ስምምነቶች እንዲደረጉ አደረገ፡፡ ኮሚኒስቶቹ እነዚህን ስምምነቶች እንዳሻቸው እየጣሱ ዳግም ለመደራጀት፣ የሶቭየት መሳርያ ድጋፍ ለማስገባት እና ጉሪላ ተዋጊዎቻቸውን ለማሰልጠን ይጠቀሙበት ነበር፡፡ ይህ የአሜሪካዊው ስራ ብሔራውያኑን አስሮ በመያዝ ኮሚኒስቶቹ ይቆጣጠሩ የነበሩትን ግዛቶች ከ57 ወደ 310 በፍጥነት እንዲያስፋፉ አስችሏቸዋል፡፡ ጀነራ ክሌር ቼኑልት የማርሻል የሰላ ስምምነት ተፅእኖን እንደሚከተለው ያብራራዋል፡
“ከሃኮው በሰሜን በኩል ወደ 200,000 የሚሆኑ የመንግስት ሰራዊቶች ወደ 70,000 የሚሆኑ የኮሚውኒስት ወታደሮችን ከበው የማጥፋት ስልታዊ ዘመቻ ጀምረው ነበር፡፡ ኮሚኒስቶቹ የሰላ ስምምነቱን በማጣቀስ ወደ ማርሻል አቤት አሉ፡፡ ይህን ተከትሎ ውግያው እንዲቆምና ኮሚኒስቶቹ ከከበባው እንዲያመልጡና ወደ ሻንቱንግ ግዛት እንዲሸሹ መንገድ ተመቻቸላቸው፣ ከአመት በኋላ ከሻንቱንግ ግዛት በመነሳት ኮሚኒስቶቹ መጠነ ሰፊ ጥቃት ጀመሩ፡፡ በምስራቅ ወንዝ ካንቶን አካባቢ ወደ 100,000 የሚጠጉ ኮሚኒስት ወታደሮች ከበባ ውስጥ ወድቀው ነበር፡፡ አሁንም የሰላም ስምምነቱ ቡድን ስራውን በመስራት ወታደሮቹ ማንም ሳይነካቸው በሰላም እንዲወጡና ወደ ቢያዝ ቤይ እንዲሄዱ አስችሏቸዋል፣ ከዚህም በመርከብ ወደ ሻንቱንግ ገቡ፡፡”
የማርሻል አውዳሚው የ 15 ወር የቻይና ተልእኮው በጥር 1947 ላይ ተገባደደ፡፡ ወደ አሜሪካ ሲመለስ ላደረሰው ኪሳራ ሁላ በፕሬዚደንቱ ትሩማን የውጭ ጉዳይ ቢሮ ዋና ፀሃፊ (ሚኒስቴር) አድርጎ በመሾም ተቀበለው፡፡ ማርሻል ብሔራውያኑ ላይ የጦር መሳርያ ማእቀብ አደረገባቸው፣ ኮሚኒስቶቹ ከሶቭየት ራሽያ መሳርያዎች እየጎረፈላቸው ማለት ነው፡፡ በኋላ ላይ ማርሻል እየተጀነነ 39 ፀረ-ኮሚኒስት ክፍለ ጦሮችን በብእሩ ጭረት ብቻ ትጥቅ እንዳስፈታ ይናገር ነበር፡፡ ይህ የቻይኖች ነፃነት ፍፃሜውን ያስያዘ ነበር፡፡

የሚድያው ሚና

ቻይናን አሳልፎ በመስጠት ዋና ሚና የነበረው የአሜሪካ ህዝብ አመለካከትን ቅርፅ ማስያዙ ነበር፡፡ የማኦ ኮሚኒስቶች ዲሞክራስያዊ ለውጥ ፈላጊ ገበሬዎች መሆናቸውን ለማሳመን የመፅሃፍ እና ጋዜጣ ፅሁፎች በብዛት ይወጡ ነበር፣ ምንም እንኳ ስልጣን በያዙ ማግስት ሁሉን አቀፍ አምባገነናዊ መንግስት በመመስት በባህል አብዮቱ ግዜ ከጫፍ የደረሰው በአስር ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ደም ቢያፈሱም ማለት ነው፡፡ ሻንግ ካይሼክ እና ብሔራውያኑ እንደ “ፋሺስት”፣ “አድሃሪያን” እና “ብልሹ” ተደርገው ሲቀርቡ ነበር፡፡
የሶቭየት ቀዳማዊ ሚኒስቴር ቭያቼስላቭ ሞሎቶቭ ስልቱን እንዲህ ሲል ያቀርበዋል፡
“የኮሚኒስት ወረቀቶችን ማን ያነባል? ኮሚኒስት የሆኑ ጥቂት ሰዎች ብቻ ናቸው፡፡ እነዚህን ደሞ መስበክ አያስፈልገንም፡፡ ዓላማችን ምንድን ነው? ማንን ነው መስበክ ያለብን? ኮሚኒስት ያልሆኑት ላይ ነው ተፅእኖ መፍጠር ያለብን፣ ኮሚኒስት ማድረግ ከፈለግን ወይም ልናታልላቸው ከፈለግን፡፡ ስለዚህ ትላቅ ፕሬሶችን ሰርገን መግባት ይኖርብናል፡፡”
ይህን ዓላማ ሲያሳኩ ከነበሩ ዝነኛ የአሜሪካ ፀሃፍያን መሃከል አንዱ ኤድጋር ስነው ይሆናል የኮሚኒስታዊው Red Star Over China የሚለው መፅሃፍ ፀሃፊ የሆነው፣ የ Thunder Out of Chinaደራሲ ኦውን ሊትሞር ይህ መፅሃፉ ሻን ካይሼክን የሚወቅስ ስራ ነው፡፡ ሳንደይ ሪቪው ላይ በሚፅፍበት ወቅት ስነው ላንባቢዎቹ፡ “በቻይና ምንም ዓይነት ኮሚኒዝም አልነበረም፡፡” ብሎ ይናገር ነበር፡፡ ሳተርደይ ኢቭኒንግ ላይ ደግሞ የማኦ ወታደራዊ አዛዥ ስለሆነው ስለ ቹ ቴ ሲፅፍ፡ “የሮበርት ኢ. ሊ ርህራሄ፣ የግራንት ቁርጠኝነት፣ እና የሊንከን ትህትና፡፡” ያለው ሰው ነው ብሎ ፅፎለታል፡፡
በትልቁ While You Slept በሚለው መፅሃፉ ጆን ቲ. ፍሊን ሚድያው ለቻይና ኮሚኒስቶቹ የሚያደርግ የነበረውን አድልዎ አሳቷል፡፡ በ 1943 እና 1949 መሃከል በምድረ አሜሪካ ኮሚኒስቶቹን የሚደግፉ 22 መፅሃፎች ታትመው ለህዝብ ቀርበዋል፣ ብሔራውያኑን የሚደግፉ 7 ብቻ ነበር የታተሙት፡፡ ፍሊን በተጨማሪም የሚከተለውን ዘግቦ ነበር፡
“ሃያ ሁለቱም ኮሚኒስቶቹን የሚደግፉት መፃህፍት ሂስ የተሰጠባቸው ሲሆኑ፣ ሁሉም አንፀባራቂ ተቀባይነት ነበር በሃያስያኑ የተሰጣቸው፣ እነዚህም በኒው ዮርክ ታይምስ፣ ዘ ሄራልድ ትሪቡን፣ ዘ ኔሽን፣ ዘ ኒው ሪፐብሊክ እና ዘ ሳተርደይ ሪቪው ኦፍ ሊትሪቸር ይገኙበታል፡፡ እነዚሁ ሃያስያን ኮሚኒስቶቹን የማይደግፉትን መፃህፍት ደግሞ በደፈናው ሲያወግዙ ወይም ሂስ ሳይሰሩ አልፈዋቸዋል፡፡”
 ኮሚኒስት ደጋፊዎቹ መፃህፍት አዋንታዊ ወይም ደጋፊ ሂስ እንዲያገኙ ያደረጋቸው ሌላኛው ምክንያት ሂስ አድራጊዎቹ ራሳቸው ተመሳሳይ ሌላ መፅሃፍት ፀሃፊዎች በመሆናቸው ነበር፡፡ ፍሊን እንደሚዘግበው ከሃያ ሁለቱ ቀይ ቻይኖቹን የሚደግፉ ፀሃፍት ውስጥ አስራ ሁለቱ የሌሎች መሰል ፀሃፍቶቻቸውን የሚያሞካሹ አርባ ሶስት ሂስ ፅፈዋል፡፡ ይህ የውስጥ ግንኙነታቸው እርስ በርስ የሚሞከሻሹባቸውን ፅሁፎች እንዲያወጡ ጠቅሟቸዋል፡፡ ስለ ኤስያ ጉዳዮች ብዙም የማያቅ ነበረውን አሜሪካዊ አንባቢን የማይጠፋ ግንዛቤ እንዲቀረፅበት አድርገዋል፡፡ ለኮሚኒስቶቹ የነበረው አድልዎ እጅግ የተጋነነ ከመሆኑ የተነሳ በኒው ዮርክ ታይምስ የሚወጡት ፅሁፎች ከኮሚኒስታዊው ደይሊ ዎርከር መፅሄት የተለዩ አልነበሩም ይለናል ፍሊን፡፡

ግልፁ ክህደት፡ አይ ፒ አር

ከሁሉየከፋው በአሜሪካ የሩቅ ምስራቅ ጉዳዮች ፖሊሲ እና አመለካከት ላይ ከፍተኛ ተፅእኖ የነበረው አሁን የፈረሰው የፓሲፊክ ግንኙነቶች ኢንስቲትዩት ነው፡፡ ከሮክፌለር እና ካርኔ ፋውዴሽኖች ፈንድ ይደረግለት የነበረው ይህ ኢንስቲትዩት በመቶዎች የሚቆጠሩ ለአሜሪካ የህዝብ ትምህርት ቤቶች እና ሰራዊቱ የሚሆኑ ወረቀቶችን በቻይና ጉዳይ ላይ አሳትሟል፡፡ እኚህ ወረቀቶች የቻይና ኮሚኒስቶች “ለውጥ ፈላጊ ገበሬዎች”፣ ብሔራውያኑ ደግሞ “ፋሺስቶች” ናቸው የሚለውን አፈ ታሪክ የሚሰብኩ ነበሩ፡፡
በኋላ ላይ የአሜሪካው ምክርቤት (ሰኔቱ) የውስጥ ደህንነት ንኡስ ኮሚቴ ባካሄደው ምርመራ አይ ፒ አር ውስጥ 54 ከዓለም አቀፋዊ የኮሚኒት ሴራ ጋር ትስስር ያላቸው ሰዎች እንዳሉበት ደርሶበታል፡፡ ከነዚህም መሃከል አልገር ሂስ፣ ፍሬደሪክ ቫንደርቢልት ፊልድ፣ ኦውን ላቲሞር፣ እና ጆን ስቴዋርት ሰርቪስ ይገኙበታል፡፡ ከኮሚኒስት ሰራዊት ያፈነገጠው ብርጋዴር ጀነራል አሌክሳንደር ባርመይን አይ ፒ አር በፓሲፊክ ለሚደረግ ወታደራዊ ስለላ ሽፋን አድርገው ይጠቀሙበት እንደነበር የምስክርነት ቃሉን ሰቷል፡፡
አይ ፒ አር አመርኤዥያ የተሰኘ መፅሄት መነረው፡፡ በ1945 ይህ መፅሄት በአሜሪካ መንግስት ጥብቅ ሚስጥራዊ የሆነ ሰነድ ቃል በቃል ገልብጦ ባሳተመበት ወቅት ብዙ ባለስልጣናትን አስደንግጦ ነበር፡፡ የኦሴስኤስ (ሲአይኤ ከመሆኑ በፊት የነበረው) ተቋም ሰዎች የአመርኤዥያን ቢሮ በመቆጣጠር ሲበረብሩ 1,800 ከአሜሪካ መንግስት የተሰረቁ ሰነዶችን ሊያገኙ ችለዋል፣ ከነዚህም በቻይና የብሔራውያኑ ጦርን ማስወገድን የሚመለከቱ ሰነዶችን ጨምሮ፡፡ ይህ መፅሄት ድብቅ የሶቭየት የስለላ ተቋም ነበር፡፡
ምንም እንኳ ኤፍቢአይ ብዙ የአመርኤዥያ መፅሄት ሰራተኞችን በስለላ ክስ ቢያስራቸውም ሁሉም ክሶች ተሰርዘዋል አልያም በገንዘብ ቅጣት ታልፈዋል፡፡ ጆን ስቴዋርት ሰርቪስ የመንግስት ሰነዶችን ለአመርኤዥያ መፅሄት ዋና አዘጋጅ ሰርቆ በመስጠት ቢከሰስም በውጭ ጉዳይ ሃላፊው ዲን ኤክሰን የስልጣን እድገት ተሰጦት የስራ ምደባ እና እድገት ክፍል ሃላፊ ተደርጓል፡፡ የተደበቁት እጆች እንዲህ ፀረ-አሜሪካ ስራ ሲሰሩ ይህ ብቸኛው ግዜ አይደለም፡፡

ለቻይና “እርዳታ”

በ1945 የጃፓን ሽንፈትን ተከትሎ በሌንድ-ሊዝ መርሃ ግብር ይጓጓዝ የተባለው ትጥቅ በህንድ አገር ተቀምጦ ለብሔራውያኑ ይዳረሳቸዋል ተብሎ የነበረው ሳይደርሳቸው የት እንደደረሰ ሳይታወቅ ቀረ፡፡ በ1948 ማርሻል ባስተላለፈው የመሳርያ ማእቀብ የብሔራውያኑ ሰራዊት ከሶቭየት መሳርያ ይሄድላቸው በነበሩት በኮሚኒስቶቹ ከመሸነፍ ጫፍ አድርሶት ነበር፡፡ የቀድሞ የዩ.ኤስ. አምባሳደር ዊልያም ሲ. ቡሊት በ1948 በውጭ ጉዳይ ኮሚቴ ፊት ቀርቦ በሰጠው ቃል የሚከተለውን ብሎ ነበር፡
“የአሜሪካ መንግስት ጀነራል ማርሻል ከነሃሴ 1946 ጀምሮ በተናጠል በወሰደው እርምጃ ለቻይና አንድም አየር ወይም ቦምብ ጣይ አውሮፕላን አልሰጠችም፣ ይህ የአሜሪካ መንግስት ለቻይና (በወቅቱ ለነበረው የብሔራውያኑ መንግስት) የገባውን ቃል ያፈረሰ ነበር፡፡ … ሻንግ ካይሼክ ላይ ኮሚኒስት ቻይኖቹን ወደ መንግስቱ እንዲያስገባ ጫና ለመፍጠር ዩናይትድ ስቴትስ የገባችውን ቃል አፍርሷል፡፡”
ዲን ኤክሰን በሃሰት ብሔራውያኑ ከአሜሪካ የ2 ቢሊዮን ዶላር እርዳታ አግኝተዋል ብሎ ምክር ቤቱን ቢዋሽም፣ አብዛኛው እርዳታ ወታደራዊ ያልነበረና ጥቅም የሌለው ነበር፡፡ ኮነሬል ኤል. ቢ. ሙዲ የዩ. ኤስ. ሰራዊት ትጥቅ አቀባይ ቡድን አባል የሆነው እውነታውን እንደሚለከተለው ያብራራልናል፡
1.      የብሄራውያኑ ሽንፈት አይቀሬ የሆነው በትጥቅ በተለይም የእግረኛ ሰራዊት ትጥቅ እጥረት ምክንያት ነበር፣ ይህን ደሞ ኮሚኒስቶቹ እንደልብ ያገኙት ነበር፡፡
2.     ወታደራዊ ድጋፍ ለቻይኖቹ ማለት በተለይ የእግረኛ ሰራዊቱ ትጥቅ ማለት ነው፡፡ ይህን ደሞ ሁሌም ደጋግመው ሲያስቀሩባቸው፣ ሲያዘገዩባቸው እና በቃ ያልሆነ መጠን ሲልኩላቸው ነበር፡፡ ብሔራውያኑን በመቶ ሚሊዮኖች እና ቢሊዮኖች የሚቆጠር እርዳታ አድርገናል እንዲባል በውጭ ጉዳይ ቢሮ ያሉ ሶሻሊስቶች ወረቀት ላይ ፅሁፋቸው እያሰፈሩ ከፓሲፊክ ደሴቶች ያገለገሉና ጥቅም የሌላቸው መሳርያዎች እና ሲጋራ እየላኩ ያታልሉ ነበር፡፡ ይላል፡፡
በሚያዝያ 1948 የሁኔታውን አሳሳቢነት በመገንዘብ ለሻንግ አስተዳደር የ125 ሚሊየን ዶላር ወታደራዊ እርዳታ እንዲደረግለት ወሰነለት፡፡ ሆኖም ግን ከዚህ እርዳታ የሚጀመርያው ዙር ብቻ እንኳ እስኪደርስ 7 ወር ፈጅቶበታ ልክ በአሜሪካ የምርጫው ግዜ ደርሶ የቻይና ጉዳይ ድምፅ ማሰባሰብያ እስከሚሆንበት ግዜ ድረስ፡፡ ከዚህ ሲነፃፀር የብሪታንያ ሰራዊት በዱንኪርክ ሽንፈት ሲደርስበት ግዜ የአሜሪካ ባህር ሃይል ትጥቅ ይዞ ለመድረስ 8 ቀን ብቻ ነበር ያስፈለገው፡፡ አንቶኒ ኩቤክ የመጀመርያው መርከብ ጭነት አርፍዶ በ1948 ለብሔራውያኑ ሲደርስ የነበረውን ሁኔታ እንዲህ ያብራራዋል፡
“ባጠቃላይ 480 አውቶማቲክ ጠመንጃ (መሺን ጋን) ይህ መለዋወጫ የሌለውና ባለ ሶስት እግሩ መቆምያ የጎደላቸው ወዘተ. ነበሩ፡፡ ቶምፕሰን መሺን ጋኖቹ ጥይት መያዣ እና ጥይት መያዣውን የሚቆልፈው ክሊፕ የሌላቸው ነበሩ፡፡ የመሳርያ መያዣ ቀበቶው ላይ መጫኛ ምንማ ዓይነት ማሽን አልነበረም፡፡ ከቀላል መሺን ጋኖቹ አንድ ሺው ብቻ እግር ነበራቸው፤ በተጨማሪም ለ 2,280 ቀላል መሺን ጋኖች የሚሆን 1,000 ክሊፕ ብቻ ነበር አብሮ የመጣው፡፡

የቻይና መውደቅ

ማእቀቡ እና ለብሄራውያኑ ኮንግረስ ይድረስ እያለ ከሚመድበው እርዳታ እየቀረ በተከተለው ኪሳራ የብሔራውያኑ ፍፃሜ አይቀሬ እንዲሆን አደረገው፡፡ በ1949 ኮሚኒስቶቹ ቻይናን ሙሉ ለሙሉ ተቆጣጠሩ፡፡ ሻንግ ካይሼክ እና ሁለት ሚሊዮን ተከታዮቹ ወደ ፎርሞሳ ዛሬ ታይዋን ወደምትባለዋ) ቦታ አመለጡ፡፡ እዚህም የቻይና ሪፐብሊክ መንግስትን ይዘው ተቀመጡ፡፡
ማኦ ሁሉን አቀፍ ኮሚኒስታዊ አምባገነን መንግስት ሲመሰርት “ለውጥ ፈላጊ ገበሬዎች” የሚለው ተረት እንደ ውሃ ተኖ ጠፋ፡፡ ኤክሰን እና በውጭ ጉዳይ ያለው ኮሚኒስት ሃዋስ ለቀይ ቻይና እውቅና እዲሰጣት ተስፋ ማድረግ ቀጠሉ፣ ሆኖም ግን የማኦ ቡድን የዩ.ሴስ. ቆንፅላ ፅፈት ቤትን በቁጥጥር ስር ሲያደርጉና፣ አሜሪካውያንን ሲያስሩ እና ሲገድሉ እና ወደ ኮርያ ዘምተው የአሜሪካ ሰራዊትን መግደል ሲጀምሩ አሜሪካ ለቻይና እውቅና ትስጣት የሚባለው ነገር ለተጨማሪ በርካታ ዓመታት እንዲራዘም ሆነ፡፡
ይህ የቻይና ውድቀት ወይም በኮሚኒስቶች እጅ መግባት በአጋጣሚ ወይም በስህተት የሆነ አይደለም፡፡ ኮንግረስማን ዋልተር ጁድ ታዋቂው የሩቅ ምስራቅ ጉዳዮች ባለ ሙያ፡ “የአማካኝ መጠን ህጎችን ብንመለከት ማንኛውም ማሰብ የማይችል  እንኳ ቢሆን አልፎ አልፎ ለአሜሪካ የሚመች / የሚያደላ ስህተት ሊሰራ ይችላል፡፡ ለኮሚኒስቶቹ የሚያደላ ፖሊሲ በአንድ ቡድን ሁሌም ሲተገበር ካየን ይህ ባጋጣሚ የሆነ ሊሆን አይችልም፡፡” ብሎ ነበር፡፡
ምንጭ፡
China Betrayed Into Communism by  James Perloff
Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s