ባራክ ኦባማ እና ሚት ሮምኒ

Posted: October 22, 2012 in ሳይንሳዊ አምባገነንነትና ፍልስፍና


በግደይ ገብረኪዳን
 ከአለማችን ትልቋ “ዲሞክራሲ”፡ ዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ በየአራት አመቱ ለምታካሂደው ፕሬዚደንታዊ ምርጫ እንደተለመደው ለማስተናገድ ሽርጉዱን ተያይዛዋለች፡፡ ይህች በአለም ዙርያ የዲሞክራሲ ፖሊስ መሆን የሚቃጣት ሃገር ይህን አጋጣሚ ተጠቅመን ዲሞክራሲዋን እንገመግምላታለን፡፡ መልካም ንባብ፡፡

ኦፊሴላዊው ልዩነት
ባራክ ኦባማ ዲሞክራት ፓርቲን ወክሎ ተፎካካሪው ሚት ሮምኒ ሪፐብሊካን ፓርቲን ወክሎ ሁለቱም ለሚወዷት ሃገራቸው ለመድከም እኔን ምረጡ ዘመቻቸውን ተያይዘውታል፡፡ በንግግራቸው እና በክርክራቸው ሁለቱም የተሸሉ እና አሜሪካ ከገባችበት ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ አጣብቂኝ እንደሚያወጡ እያሳወቁ ይገኛሉ፡፡ እስካሁን በቀጥታ ተለቪዥን የተሰራጨ ሁለት ክርክር ያደረጉ ሲሆን በመጀመርያው ሮምኒ በሁለተኛው ኦባማ የበላይነትን አግኝተዋል፡፡ አሁን አለን የሚሉትን ልዩነቶች ከአንደበታቸው እንደሰሙን እና መገና ብዙሃን አሳጥረው እንዳስረዱን እናቀርበዋለን፡፡
ልዩነታቸው በአንኳሩ ያየነው እንደሆነ እነሱ እንደሚሉት ከሆነ ኦባማ ወደ ሊበራሎች ሮምኒ ደሞ ወደ ወግ አጥባቂዎቹ ያዘመሙ ናቸው፡፡ ሊበራል ማለት በሃገራችን ስማቸው አስሬ እንደሚነሳው መንግስት እጁን ይሰብስብ ህዝብ እና ቢዝነስ እንዳሻው ይፈንጭ የሚሉ አይደሉም፡፡ አሁን ያሉት ሊበራሎች ፍልስፍና ፕራግማቲዝም ወይም ተጋባራዊነት የሚመራቸው ሲሆን አብዛኛው ፖሊሲያቸው እንዲያውም በማህበራዊ ዋስትና ስም ውደ ሶሻሊስቶች የተጠጋ ነው፡፡ ወግ አጥባቂዎች ደሞ በሃይማኖተኝነታቸው እንዲታወቁ የሚፈልጉ ሲሆን ሶሻሊዝምን እንደ ምድራዊ ገሃነም ያዩታል፡፡ ሆኖም እነዚም ቢሆን ተግባራቸው “ነን” ወይም “ናቸው” ከሚባልላቸው ተቃራኒ ናቸው፡፡ አሁን እስኪ ኦባማ እና ሮምኒ አለን የሚለን የሚሉትን የፖሊሲ ልዩነት እንዳስስ፡፡
ኢኮኖሚ
ኦባማ፡ ቡሽ ያስተዋወቀውን ከ250,000 ዶላር በላይ አመታዊ ገቢ ላላቸው የግብር እፎይታን ማንሳት፡፡ በአምራች ኢንዱስትሪ ላይ ያለውን ግብር መቀነስ፡፡ ኢኮኖሚውን ለማነቃቃት ለአጭር ግዜ የማነቃቅያ ወጪ ማፍሰስ እና ግብር መቀነስ፡፡ የበጀት ጉድለቱን ለመቀነስ ሃብታሞች ላይ ግብር መጨመር እና የመንግስት ወጪዎችን መቀነስ፡፡
ሮምኒ፡ የቡሽ የግብር እፎይታን ቋሚ ማድረግ፡፡ ኮርፖሬሽኖች የሚከፍሉትን ግብር 25 መቶኛ መቀነስ፡፡ ቢዝነስ ለማበረታታት ግብር መቀነስና ቁጥጥር ማላላት፡፡ ከደህንነት ጋር ያልተያያዘ የመንስት ወጪን 5 መቶኛ መቀነስ፡፡
ጤና
ኦባማ፡ በ2010 አዲስ የጤና ፖሊሲ የፈረመ ሲሆን የጤና ኢንሹራንስ ሽፋኑን ማስፋት፡ ቀጣሪው ሰራተኛውን ከመቅጠሩ በፊት ለነበሩ ህመሞችም እንዲሸፍን ማድረግ፡፡ ሲታመሙ ዋስ የገቡት ዋስትና መሰረዝን ማገድ፡፡ እናም ሁሉም ጤና ኢንሹራን እንዲገዛ ካልሆነ ቅጣት እንዲከፍል ያደርጋል፡፡
ሮምኒ፡ የማሳቹሴትስ ገዢ እያለ ተመሳሳይ ህግ ያስፀደቀ ሲሆን አሁን ግን እንዲህ ዓይነት ፖሊሲ በመላው አሜሪካ መጫን ልክ አይደለም ይላል፡፡ ከአሰሪዎቻቸው ይልቅ ሰዎች በግላቸው ዋስትና እንዲገዙ ይደግፋል፡፡
ስደተኞች፡
ኦባማ፡ ሁሉም ህገ ወጥ ስደተኞች ህጋዊ እንዲደረጉ እና እግሊዘኛ እንዲማሩና የቅጣት ክፍያ እንዲከፍሉ ይላል፡፡ ህገወጦችን የሚያሰሩ ላይ ቅጣቱን ማበርታት፡፡ የሜክሲኮ ድንበር እንዲታጠር ድምፅ ሰቷል፡፡ የተወሰኑ ህገ ወጥ ስደተኞች ተመላሽ እንዳይደረጉ የመጨረሻ ትእዛዝ (ኤክዝኪዩቲቭ ኦርደር) ፈርሟል፡፡
ሮምኒ፡ እንግሊዘኛ የዩ.ኤስ.ኤ. ኦፊሴላዊ ቋንቋ እንዲሆን እና ወደ ሃገሪቱ ሰዎች እንዲገቡ የሚያደርጉ ነገሮችን እንደ ቲዩሽን ብሬክ የመሳሰሉ ፖሊሲዎችን ህገ ወጥ ማድረግ፡፡
በኢራቅ ዙርያ፡
ኦባማ፡ ወረራን አይደግፍም፣ በዛ ያሉትን ሰራዊት ቁጥር መጨመር አይደግፍም፣ በኢራቅ የነበረውን ወታደራዊ ዘመቻ አቋርጧል (ይህ የሆነው ግን ቀድሞኑ ቡሽ ባወጣው መርሃ ግብር ተከትሎ ነበር) በ2009 ወታሮችን አስወጣለው ያለውን ቃል የውሃ ሽታ ነበር የሆነው፡፡ ወራዊቶቹን ወደ አፍጋኒስታን እና ኢራን ድንበር አስጠግቷል፡፡
ሮምኒ፡ በደፈናው ሰራዊቱን በኢራቅ ማቆየት ጉዳቶችን ለመቀነስና በኢራቅ “ዲሞክራሲን” ለመጠበቅ ጠቃሚ ነው ይላል፡፡
በኢራን ዙርያ
ኦባማ፡ ቀጥተኛ ውይይትን ይደግፋል፣ ከዓለም አቀፋዊ ትብብር ጋር ማእቀቦችን እያከረሩ መሄድ፣ ወታደራዊ እርምጃ ከጠረጴዛው ላይ አልተወገደም፡፡ በ2008 ምርጫ ዘመቻ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ከኢራኑ መሪ ጋር ለመገናኘት የገባውን ቃል አልፈፀመም፡፡
ሮምኒ፡ ወታደራዊ እርምጃ ከጠረጴዛው ላይ አልተወገደም፡፡
በአለም ሙቀት መጨመርና ስነ ምህዳሩ ዙርያ
ኦባማ፡ ካርቦን ልቀትን ለመቀነስ ገንዘብ ቅጣትና ማበረታቻ ፖሊሲ ይደግፋል፡፡ የኪ ስቶን ኤክስ ኤል የነዳጅ ትቦ ዝርጋታን ውሳኔ በአካባብያዊ ጥያቄ ምክንያት ውሳኔ አራዝሟል፡፡
ሮምኒ፡ ገንዘብ ቅጣትና ማበረታቻ ፖሊሲን ይቃወማል፡፡ የኪ ስቶን ኤክስ ኤል ትቦ ዝርጋታውን ይደግፋል፡፡ ካርቦን ልቀትን ወደ ቻይና ኤክስፖርት ማድረግ አሜሪካ እና ምድሪቱን ይጎዳል ይላል(2007)፡፡ የሰው ልጆች የዓለም ሙቀት መጨመር አስተዋፅኦ አላቸው ይላል(2011)፡፡ 20 ቢሊዮን ዶላር የሚፈጅ የሃይል እና አዲስ መኪና ቴክኖሎጂ ምርምር እቅድ አለው፡፡
ሰዎችን ያለፍርድ ቤት ትእዛዝ ለፈለገው ግዜ መያዝ (Indefinite detention)
ኦባማ፡ በህዝባዊ ንግግሩ የሚቃወመው ሲሆን፣ በምክርቤቱ ወለል ላይ ግን አስተዳደሩ እንዲህ ዓይነት ህግ ለማስፀደቅ በሚደረገው ጥረት “ከአሜሪካውያን በስተቀር” የሚለው ሃረግ ምክር ቤቱ እንዲሰርዘው ጠይቋል፡፡
ሮምኒ፡ ህጉን ይደግፈዋል፡፡
ወታደራዊ ጣልቃ ገብነትን በተመለከተ
ኦባማ፡ በህዝብ እውቅና ደረጃ ጦርነቶችንና ጣልቃ ገብነትን ይቃወማል፣ በቅርቡ ግን የአፍጋን ጦርነቱን ወደ ፓኪስታን ማስፋፋት እቅዱን ተናግሯል፡፡ የተባበሩት መንግስታት ይሁንታውን ከሰጠ የአሜሪካ ምክርቤት ድምፅ አያስፈልግም ይላል፡፡
ሮምኒ፡ ህግ ሙያተኞችን ማማከር እንዳለበት የሚናገር ሲሆን ፕሬዚደንቱ ግን አሜሪካን ደህንነት ለማስጠበቅ አስፈላጊውን ሁሉ ማድረግ ይችላ ይላል፡፡
በግብረሰዶማውያን ዙር
ኦባማ፡ የተመሳሳይ ፆታ ጋብቻን ይደግፋል፣ ግብረ ሰዶማውን በግልፅ በሰራዊቱ እንዲያገለግሉ ምክርቤቱ ፈቃዱን እንዲሰጥ ጠይቋል፡፡
ሮምኒ፡ የተመሳሳይ ፆታ ጋብቻን ይቃወማል፣ በሰራዊቱ ማገልገላቸውን የማይቃወም ሲሆን፣ በስራ ቦታ የነሱ መገለልን የሚቃወም እንቅስቃሴን ሲደግፍ ነበር፡፡ ብዙ ግዜ የሚቀያየር አቋም ያለው ሲሆን ይደግፋል ቢባል ይቀል ነበር ግን እንደማይደግፍ ይናገራል፡፡
ፅንስ በማስወረድ ዙርያ
ኦባማ፡ ውርጃን ይደግፋል፡፡
ሮምኒ፡ ክፍለ ሃገራቱ ውርጃን ህገ ወጥ የማድረግ መብታቸውን ይደግፋል፡፡ እ.ኤ.አ. በ1994 የማስወረድ መብትን የሚደግፍ ህግ ያስፀደቀ ሲሆን በግል ግን እቃወማለው ይላል፡፡ ከፊል ውርጃን የሚደግፍ ሲሆን እ.ኤ.አ. ከ2005 ጀምሮ ግን ሙሉ ተቃዋሚ ሁኗል፡፡
የፃፏቸው መፃህፍት
ኦባማ፡ Dreams from My Father: A story of Race and Inheritance; እና The Audacity of Hope: Thoughts of Reclaiming the American Dream
ሮምኒ፡ No Apology: The Case for American Greatness; እና Turnaround: Crisis, Leadership, and the Olympic Games
ከመጋረጃው በስተጀርባ፡ የምር ኦባማና ሮምኒ ይለያያሉ?
የተባለው ተባለና እንኳን በፖለቲካው ቀርቶ በሌላ በማንኛውም ህይወት ዙርያ በጋህድ በመድረክ ሁሉም ተውኔቱን ካሳየን በኋላ ከመጋረጃው ጀርባ ሲሆኑ ግን የማንታዘባቸው ክስተቶች ይቀጠላሉ፡፡ ከላይ ያየነውን መረጃቸውን ተጠቅመን ስንተነትን ኦባማ ከተመረጠ፡ ከሶርያ፣ ከኢራን ቀስ ብሎ ደሞ ሩስያ እና ቻይና ጋር ጦርነት የማይቀር ነው፡፡ ኢኮኖሚውም ቁልቁል መውረዱን ይቀጥላል፣ ይህም የድምበር ዘለል ፊናንሳዊ ኮርፖሬሽኖች ትርፍን ይጨምራል፡፡ ሮምኒ ከተመረጠ ግን ከሶርያ፣ ከኢራን ቀስ ብሎ ደሞ ሩስያ እና ቻይና ጋር ጦርነት የማይቀር ነው፡፡ ኢኮኖሚውም ቁልቁል መውረዱን ይቀጥላል፣ ይህም የድምበር ዘለል ፊናንሳዊ ኮርፖሬሽኖች ትርፍን ይጨምራል፡፡ ለምን?
ምክንያቱም ዋይት ሃውስ በዎል ስትሪት እና ለንደን የሚገኙ  ፊናንሳዊ ኮርፖሬሽኖች የህዝብ ግንኙነት መድረካቸው ከሆነ ከርሟል፡፡ በዋይት ሃውስ የገባው ሰው ቢቀያየር ለውጥ የለውም፡፡ ይህም የሚባልበት ምክንያት ወደ ዋይት ሃውስ እንዲገቡ የምረጡኝ ዘመቻቸውን የሚደጉሙት ኮርፖሬሽኖች ስም፣ ፖሊሲ ጉዳዮች የሚያማክሯቸው እና የሚፅፉላቸው ሰዎች ምንነት በሚፈተሸበት ግዜ ከአስተዳደር ወደ አስተዳደር የማይቀየሩ ሁነው ስለሚገኙ ነው፡፡
ቡሽ = ኦባማ = ሮምኒ
ኮርፖሬት ሚድያው እን ፈንቶ ልዩነቶች ላይ በማተኮር ሲለፍፍ እና ፖለቲካ “ተንታኞች” ማይረባ “የቀኝ” እና “ግራ” ዘመም ልዩነቶችን ሲያስተምሩን ጠለቅ ብለን የመረመርን እንደሆነ ግን የፕሬዚደንቶቹ ካቢኔዎች፣ የሃገራዊ እና ውጭ ፖሊሲ ቀራጮቹን ያየን እንደሆነ “ቡሽ = ኦባማ = ሮምኒ” የሚለው የእኩልነት ማሳያ ስሌት ምን ያህል ፍፁም ትክክል እንደሆነ እናውቃለን፡፡
ለ100 ዓመት በፊት ከባለፀጋው ከጄ.ፒ. ሞርጋን ዘመን ጀምሮ ሃብታሞቹ እራሳቸውን ከመንግስት በላይ አድርገው በመቁጠር መንግስትንና ብሔራዊ ሉአላዊነትን እንደ እንቅፋት የሆኑ ቁጥጥሮች በመቁጠር በጉትጎታ (ሎቢ)፣ በጉቦ እና በሌሎች ስልቶች ህልውናቸውን ለመገርሰስ እንደሚሰሩ የታወቀ ነው፡፡ ባለፉት 100 ዓመታት የባለፀጋዎቹ መደብ የፕሬዚደንት ቢሮውን በቁጥጥራቸው ስር በማስገባት እንደ ህዝብ ግንኙነት ቢሯቸው አድርገውታል፡፡ የፈለጉትን ያሳውጁበታል፡፡
ጆርጅ ቡሽ
የጆርጅ ቡሽ ካቢኔት ከፌዴክስ፣ ቦይንግ፣ ከአንደኛ ዓለም ጦርነት በኋላ በቁንጮዎቹ የተመሰረተው የውጭ ጉዳይ መማክርት (ሲ.ኤፍ.አር.)፣ የትላልቅ ነዳጅ ድርጅቶቹ ተደጓሚ የሆነው ሃርቫርድ የሚገኘው ቤልፈር ማእከል፣ ስትራቴጂያዊ እና አለም አቀፍ ጥናት ማእከል (ሲ.ኤስ.አይ.ኤስ.)፣ ሰርኪዩት ሲቲ፣ ቨሪዞን፣ ሰርበረስ ካፒታል ማኔጅመንት፣ ጎልድማን ሳክስ እና ራንድ ኮርፖሬሽን ወዘተ. የመጡ ሰዎች የተሰባሰቡበት ነበር፡፡
ከላይ በምስሉ እንደሚታየው የሄነሪ ጃክሰን ሶሳይቲ ደሞ አዲሶቹ ወግ አጥባቂዎች ከሚባሉት ቲንክ ታንኮች (ምርምር ተቋማት) አንዱ ነው፡፡ በዚህ ተቋም እኚሁ ሰዎች እና ኮርፖሬት ስፖንሰሮች ይገኛሉ፡፡ የተለያዩ የምርምር ተቋማት በህዝብ ያላቸው እይታ እና አትኩሮት የሚያደርጉበት የምርምር ዘርፍ የሚለያይ ሲሆን በውስጣቸው ግን አንድ አይነት ግለሰቦችንና ኮርፖሬት ስፖንሰሮች ያንቀሳቅሷቸዋል፡፡
ቡሽ የውጭ ፖሊሲው በነዚህ የአዲሶቹ ወግ አጥባቂዎች ማለትም ሪቻርድ ፐርሊ፣ ዲክ ቼኒ፣ ዶናልድ ራምስፊልድ፣ ጄን ኪርክፓትክ፣ ፖል ዎልፍዊትዝ፣ ጄምስ ዉልሴይ፣ ሪቻርድ አርሚቴጅ፣ ዛለመይ ካሊለዛድ፣ ኢልት አብራሃም፣ ፍራንክ ጋፍኔ፣ ኢልዮት ኮኸን፣ ጆን ቦልተን፣ ሮበርት ካጋን፣ ፍራንሲስ ፉኩያማ፣ ዊልም ክሪስቶል እና ማክስ ቡት የመሳሰሉትን ያካተተ ቡድን ነበር ያረቀቀው፡፡ እኚህ ሁሉም ሰዎች አስካሁን ድረስ “የሊበራሎቹን” አስተዳደር ሳይቀር ፖሊሲ የሚያረቁትን ኮርፖሬሽኖቹ በሚደግሟቸው የምርምር ተቋማት ውስጥ ተቀማጭነት አላቸው፡፡ ከነዚህም ተቋማት ውስጥ፡ ብሩኪንግስ ኢንስቲትዩሽን፣ ኢንተርናሽናል ክራይስስ ግሩፕ፣ ፎረይን ፖሊሲ ኢንሽኤቲቭ፣ የሄነሪ ጃክሰን ሶሳይቲ፣ የውጭ ግንኙነት መማክርት እና ሌሎችም መጥቀስ ይቻላል፡፡
ከላይ በምስሉ አንዳንድ የብሩኪንግስ ኢንስቲትዩሽን ስፖንሰሮች ይታያሉ፡፡ ይህ ተቋም ለብቻውን የሚነጠል ሳይሆን በአጠቃላይ በአሜሪካ ያለውን የኮርፖሬሽኖች እና በምርምር ተቋማት መሃል ያለውን ትስስር ማሳያ አብነት ነው፡፡ ካቢኔ ወንበር የሚይዙትም በነዚህ ተቋማት እያሉ የፃፉትን ወረቀት ማህተም አድረገው ፖሊሲ ያርጉታል፡፡
ባራክ ኦባማ
የኦባማ ካቢኔትም ቢሆን ከጄ.ፒ. ሞርጋን፣ ጎልድማን ሳክስ፣ የውጭ ጉዳይ መማክርት፣ የኮርፖሬሽኖቹ ተወካይ ኮቪነርግቶንና በርሊንግ፣ ሲቲ ግፕ፣ ፍሬዲ ማክ፣ የመከላከያ ኮንትራቶች የሚሰጡት ሃኒዌል የተወከሉ ሰዎች ይገኙበታል፡፡ እንደቡሽ ካቢኔት የውጭ ጉዳ ፖሊሲዎች ኦባማ በእንቁላል ቅርፅ ባለው ቢሮው ጠረጴዛ ተቀምጦ በሚፅፋቸው ወረቀቶች የሚመራ አይደለም፡፡ እኚሁ የቡሽ አስተዳደርን ሲመሩ የነበሩ የምርምር ተቋማት፡ የውጭ ጉዳይ መማክርት፣ ራንድ ኮርፖሬሽን፣ ብሩኪንግስ ኢንስቲትዩሽን፣ ኢንተርናሽናል ክራይስስ ግሩፕ እና ቻንታም ሃውስ ናቸው አሁንም በኦባማ አስተዳደር ዋናውን ሚና የሚጫወቱት፡፡  በተጨማሪም ህልቆ መሳፍርት የሆኑ እኚሁ ሰዎች የሚያንቀሳቅሷቸው እኚሁ ኮርፖሬሽኖች ስፖንሰር የሚያደርጓቸው በተለያየ ዘርፍ የሚያተኩሩ ጥቃቅን ተቋማት ይገኛሉ፡፡  

ከላይ በምስሉ የሚታዩት የኦባማ ካቢኔ ስፖንሰሮች ናቸው፣ ያለፈውንና አሁን ያለውን ትስስር ያሳያል፡፡ እንደሚታየው እዚህ ያሉት በቡሽ አስተዳደርም ነበሩ፡፡

ሚት ሮምኒ
አሁን ደሞ ሮምኒ ፕሬዚደንታዊ “ፉክክር” ውስጥ ሁኖ ኦባማን በሚፎካከርበት ግዜ፡፡ የውጭ ፖሊሲ አማካሪዎቹ ምንነቱን ፍንትው አድርገው ያሳዩናል፡ ማይክል ቼርቶፍ፣ ኢልዮት ኮኸን፣ ፓውላ ዶብረይንስኪ፣ ኤሪክ ኤደልማን እና ሮበርት ካጋን ያው ቡሽን እና ኦባማን ሲያማክሩ የነበሩትን ኮርፖሬሽኖቹ የሚደጉሟቸውን ምርምር ተቋማትን ይወክላሉ፡፡
ቡሽ እና ኦባማ የምእራቡን ወታደራዊ የመስፋፋት እንቅስቃሴን በአጋጣሚ የተነሱ ቀውሶች ውጤት አድርገው የሚያቀርቡ ሲሆን በእውነቱ ግን ቢያንስ እ.ኤ.አ. ከ1991 ዓ.ም ጀምሮ ኢራቅ፣ ኢራን፣ አፍጋኒስታን፣ ሶርያ፣ ሊብያ፣ ሱዳን፣ ሶማልያ እና ሌሎችም በሶቭየት ተፅእኖ ስር የነበሩ ሃገሮች ቀድሞኑ ለፖለቲካዊ ቀውስና መንግስት ቅየራ ወይም ግልፅ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት የታጩ ሃገሮች ነበሩ፡፡ ህዝቡ “ሽብር ላይ በታወጀ ጦርነት” ስም ቡሽ ለምን  ሁለት ሃገሮች ላይ እንደዘመተ የተለያየ ትንታኔ ሲሰጠው እና በኦባማ ግዜ ደሞ እነዚህን አስፋፍቶ አዳዲሶች በሊብያ እና ሶርያ ተሳትፎ ሌሎችም አገሮች ሲታቀድላቸው ስንሰማ “የአጀንዳዎች መቀጠል” እንጂ መቀያየር አላየንም፡፡ እኚህ አጀንዳዎች የኮርፖሬሽኖቹ ናቸው እንጂ የአሜሪካ ህዝብን ሁነ ብሔራዊ ጥቅምን አይወክልም፡፡
ከላይ በምስሉ የኢንተርናሽናል ክራይስስ ግሩፕ ኮርፖሬት ስፖንሰሮች ግዙፍ ዓለም አቀፋዊ ተቋሞች ሲሆኑ የአሜሪካን ብቻ ሳይሆን የአውሮፓንም የውጭ ፖሊሲ የሚያሾሩ እና በተግባር የሚፈፅሙ ናቸው፡፡ የኢንተርናሽናል ክራይስስ ግሩፕ የበላይ ጠባቂ የቀድሞው የተባበሩት መንግስታት ዋና ፀ ሃፊ የነበረው ኮፊ አናን ነው፡፡ ባለፈው በኔቶ ደጋፊነት ከሶርያ እና ከሶርያ ውጭ የተሰባሰቡ አሸባሪዎችን እና የሶርያ መንግስትን ለማወያየት ኮፊ አናን ተልእኮ ይዞ ወደ ሶርያ ተጉዞ ነበር፡፡ ይህ ሁሉ ሰላም ለማስፈን በሚል ሽፋን ነው፡፡  

ባራክ ኦባማን እና ሚት ሮምኒን አንድ የሚያደርጉ ነጥቦች
1.      ባራክ ኦባማና ሚት ሮምኒ ሁለቱም የታርፕ (Troubled Asset Relief Program) ይደግፋሉ፡፡
2.     ሮምኒ የባራክ ኦባማን ኢኮኖሚ ማነቃቅያ እንቅስቃሴዎችን ይደግፍነበር፡፡
3.     ሚት ሮምኒ የባራክ ኦባማ የመኪና ኢንዱስትሪዎቹን ድጎማ ፖሊሲ መጀመርያ የኔ ሃሳብ ነበር ብሏል፡፡
4.     ሁለቱም ተፎካካሪዎች የፌደራል በጀቱን ሚዛን ባስቸኳይ ማስተካከል አይደግፉም፡፡
5.     ሁለቱም ይበልጥ የመንግስት እጅ ጣልቃ ገብነትን የሚደግፉ ሲሆን ሁለቱም በያዟቸው ቢሮዎች ከፍተኛ ገንዘብ በማፍሰስ ይታወቃሉ፡፡
6.     ሁለቱም የፌደራል ሪዘርቭ (የአሜሪካ የግል ማእከላዊ ባንክ) ደጋፊዎች ናቸው፡፡
7.     ሁለቱም ፕሬዚደንት በፌደራል ሪዘርቭ ጣልቃ መግባት የለበትም ብለዋል፡፡
8.     ሁለቱም በፋይናንሳዊ ቀውስ ግዜ የሪዘርቩ ሊቀ መንበር ቤን በርናንኬ ጥሩ ስራ ነው የሰራው ብለዋል፡፡
9.     ሁለቱም ቤን በርናንኪ ተጨማሪ ዘመን ማገልገል አለበት ብለዋል፡፡
10.    ሁለቱም የፌደራል ሪዘርቭ ኦዲት መመርመርን ይቃወማሉ፡፡
11.     ሁለቱም የገንዘብ ሚኒስተርሩ (ትሬዠሪ ሴክረታሪ) ቲሞቲ ጋየትነር ጥሩ ስራ ሰርቷል ብለዋል፡፡
12.    ሁለቱም የዩኒቨርሳል ጤና አገልግሎት ደጋፊዎች ናቸው፡፡
13.    አሁን ኦባማ ኬር እየተባለ የሚቃወመውን የጤና ፖሊሲ ቀድሞ ያዳበረው እና የተገበረው ሚት ሮምኒ ነው፡፡
14.    ዎል ስትሪት ሁለቱንም እጩዎች በገንዘብ ያንበሸብሻቸዋል፡፡
15.    ሁለቱም የገቢ ግብርን ወይንም ገቢ ግብር ሰብሳቢውን ማስወገድ አይደግፉም (ይህ ግብርና ተቋም በአሜሪካ ህገ መንግስታዊ መሰረት የለውም፡፡)
16.   ሁለቱም ለብዙሃን አሜሪካውያን የሚከፍሉትን የግል ገቢ ግብር ክፍያ መጠን አንድ አይነት ነው፡፡
17.    ሁለቱም የቫት ክፍያንይደግፋሉ፡፡
18.    ሁለቱም የትራንስፖርት እና ደህንነት ባለስልጣኑ ጥሩ ስራ እየሰራ ነው ይላሉ፡፡
19.   ሁለቱም የኤን.ዲ.ኤ.ኤ. (National Defense Authorization Act) ደጋፊዎችናቸው፡፡
20.   ሁለቱም በቡሽ ግዜ ስንት ውዝግብ ፈጥሮ የነበረውንና የአሜሪካን ህገ መንግስት የሻረ ነው የተባለውን የአርበኛ አዋጅ ዳግም መፅደቅን ይደግፋሉ፡፡
21.    ሁለቱም የአሜሪካ መንግስት አሸባሪ ናቸው የተባሉ ዜጎችን ያለምንም ገደብ ያለ ፍርድ ቤት እውቅና በእስር ማቆየት ይደግፋሉ፡፡
22.   ሁለቱም አሸባሪ ነው የተባለ ዜጋን በፕሬዚደንቱ ትእዛዝ ብቻ ያለ ፍርድ ቤት እውቅና መግደል ይቻላል ይላሉ፡፡
23.   ባራክ ኦባማ ቃል እንደገባው ጓንታናሞ ቤይን አልዘጋም፣ ሚት ሮምኒ ደሞ እዛ ያሉትን እስረኞች በእጥፍ መጨመር ይፈልጋል፡፡
24.   ሁለቱም ወንጀለኛ ነው የተባለን ያለ ፍርድ ቤት ትእዛዝ ለሌላ አገር አስተላፍ መስጠትን ይደግፋሉ፡፡
25.   ስራ አጥነትን እና ተገቢ ያልሆነ ውድድርን የሚፈጥረውን ነፃ ንግድን ሁለቱም ይደግፋሉ፡፡
26.  ሁለቱም ስራ እድል ፈጠራ ከሃገር ውጭ እንዲወጣ በማድረግ ይወነጃጀላሉ፡፡ (ሁለቱም ልክ ናቸው፡፡)
27.   ሁለቱም በህገ ወጥ ስደተኞች ዙርያ ልል አቋም ያራምዳሉ፡፡
28.   ሁለቱም ምንም ወታደራዊ ልምድ የሌላቸው ሲሆኑ፣ ከ1944ጀምሮ ይህ የሆነበት በታሪክ ለመጀመርያ ግዜ ነው፡፡
29.  ሁለቱም ዲግሪያቸውን ያገኙት ከሃርቫርድነው፡፡
30.   ሁለቱም የዓለም ሙቀት መጨመር ሰው ሰራሽ ነው የሚለውን ንድፈ ሃሳብ ያምናሉ፡፡
31.    ሚት ሮምኒ ሁሉም የዓለም ሃገሮች የሚደግፉት ከሆነኦባማ የሚያካሂደውን የካርበን ልቀት ንግድን (በገንዘብ መቅጣትና መሸለም) እደግፋለው ብሏል፡፡
32.   ሁለቱም ጥብቅ የሆነ የመሳርያ ቁጥጥር ፖሊሲዎችን ያራምዳሉ፡፡
33.   ሁለቱም የፅንስ ማስወረድ ደጋፊዎች ናቸው፡፡ ሚት ሮምኒ አሁን መቀየሩ ብዙዎችን እያነጋገረ ነው፣ እንድያውም ሚት ሮምኒ በይንስ ካፒታል በሚባል ድርጅት አማካኝነት “ስቴሪሳይክል” በተሰኘ ድርጅት ውስጥ ባለው ኢንቨስትመንት ሚሊዮኖችን አትርፏል፡ ድርጅቱ የተጨናገፉ ልጆችን በእሳት በማቃጠል የሚያስወግድ ነው፡፡
34.   ሁለቱም በግብረ ሰዶማውያን ወታደሮች ላይ ያለው እገዳን ይቃወማሉ፡፡
35.   ሁለቱም በእስራኤል እና በፍልስጤም መካከል ዘላቂ ሰላም የሚያመጣው “የሁለት መንግስታት መፍትሄ” ነው ብለው ያምናሉ፡፡
36.  ሁለቱም እጅግ ሊበራል የሆኑ ዳኞችን በመሾም ይታወቃሉ፡፡
37.   እንደ ኦባማ ሁሉም ሮምኒም ህግ ፀድቆ ሲፈርም ትርጉሙኑም አብሮ መፃፍ ማለትም signing statementsይደግፋል፡፡ ይግ በአሜሪካ ህገመንግስታዊ መሰረት የለውም፣ ፕሬዚደንቱ የህግ ተርጓሚነት ሚናን ሊጫወት አይችልም፡፡
38.   በስራ ፈጠራ ዙርያ ሁለቱም አስከፊ መዝገብ አላቸው፡፡
39.  ሁለቱም ያለምክር ቤቱ ፈቃድ ፕሬዚደንቱ ብቻ ሃገሪቱን ወደ ጦርነት ማስገባት ይችላል ብለው ያምናሉ፡፡
40.   ሁለቱም የአሜሪካ መንግስት እዳን መቆለሉን መቀጠሉን ያምኑበታል፣ ምንም እንኳ በአሁኑ ግዜ የመንግስታቸው እዳ 16 ትሪሊዮን ዶላር ቢደርስም፡፡
መደምደምያ
ማንም በ2012 የአሜሪካ ምርጫ ቢያሸንፍ የኮርፖሬሽኖቹ ተፅእኖ እንዲወገድ ካልተደረገ፣ የፈለገውን አጀንዳ ለህዝቡ ቃል ቢገባ የሚለወጥ ነገር አይኖርም፡፡ ሮምኒ ቢመረጥ ኦባማ የጀመረውን ነው የሚያስቀጥለው ልክ ኦባማ ቡሽ ያስጀመረውን እንዳስቀጠለ፡፡ ሁሉም ቀደርሞ የነበረው ካቆመበት ነው የሚቀጥለው፡፡ አሜሪካ እያሾሯት ያሉት ትላልቅ ድርጅቶች ናቸው፡ እ.ኤ.አ. የአሜሪካ ባህር ሃይል ጀነራል የሆነው ጀነራል ስሚድሊ ባትለር “War is a Racket” በሚለው አጭር መፅሃፉ ጉዳዩን አጋልጦታል፡፡
የአሜሪካ ህዝብ አሁን ነገሮች በስህተት ጎዳና እንዳሉ እየታዘበ ነው፡፡ ኮርፖሬሽኖቹም ለውጥ እንዳይመጣ አጥብቀው እየሰሩ ነው፡፡ ችግሮችን እየፈጠሩ እና ለግላቸው የሚጠቅም የማይሆን መፍትሄ እያቀረቡ ህዝቡ ዋናው ችግሩን እንዳይፈታ በያቅጣጫው እየበተኑት ይገኛሉ፡፡  
Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s