የሰብአዊነት የ 5000 ዓመታት ጉዞ (ካልታተመ መፅሃፍ የተወሰደ በግደይ ገ/ኪዳን እና ተክሉ አስኳሉ)

Posted: March 9, 2012 in ሳይንሳዊ አምባገነንነትና ፍልስፍና
21
የሰብአዊነት የ 5000ዓመታትጉዞ
ሰብአዊነት የሚለው ቃል ስለ ሰው ልጅ መቆርቆርን የሚያመላክት ቃል እንደመሆኑ ከየትኛውም በጎ እሴት ጋር ሊቆራኝ ይችላል፡፡ ሰብአዊነት የተሰኘውን ፍልስፍናዊ ሃይማኖት ማስረዳት ከመጀመራችን በፊት በቅድሚያ የቃሉን አሻሚ ትርጉም መለየት ይኖርብናል፡፡ የሰብአዊነት ፍልስፍና እና ሰብአዊ እርዳታ አብረው የማይሄዱ እሳትና ጭድ ናቸው፡፡ ሰብአዊ እርዳታ ማለት አንድ ሰው ለባልንጀራው የሚያሳየውን ርህራሄ ወይም ደጋፊነትን የሚገልፅ ሲሆን ሰብአዊነት የተሰኘው ፍልስፍና በአንፃሩ ሰውን ማእከል ያደረገ የዓለም እይታ ነው፡፡ ሰውን ማእከል ማድረጉ መልካም ቢመስልም የዚህ እንደምታ መዘዝ ሲመረመር ማር የተቀባው መርዝ መገለጥ ይጀምራል፡፡
ሰብአዊነት ከሃይማኖታዊ ወይም ከሰማያዊ እሴቶች ይልቅ የሰው ልጅ ተፈጥሯዊ እምቅ ሃይሎችን ማመን የሚሰብክ ነው፡፡ ሰብአዊነት ከሰማያዊ ወይም ረቂቅ እሳቤዎች ይልቅ ለሰው ልጆች ምድራዊ ጉዳዮች የላቀ ቦታ የሚሰጥ ሀሳብ ነው፡፡ ስለዚህም ይህ አመክንዮን (reason) ብቻ በመጠቀም እራስህን ማግኘት (self-realisation ) ላይ የሚያተኩር ዶግማ ነው፣ ምክንያቱም የትኛውንም ሃይማኖታዊ ወይም ሰማያዊ (supernatural) እምነትን የማይቀበል ነውና፡፡ አመክንዮ መሰረተ-እውነትን (ሎጂክ) በመጠቀም ድምዳሜ ላይ ለመድረስ የሚደረግ ሂደት ነው፣ እናም የሰው ልጅን የአመክንዮ እንሰሳ ነው ስንል ሰው ከእንስሳት የሚለየው ማስረጃዎችን በመጠቀም ውሳኔ ላይ የመድረስ ችሎታው ብቻ ነው እያልን ነው፡፡ ሰብአውያንም ይህንን ችሎታውን ከማይነቀፍ የቅዱስነት መአርግ ደረጃ ይሰቅሉታል፡፡  ስለዚህም ሰብአዊነት ዓለምን በሰው ልጅ ፍላጎቶች ወይም እሴቶች ላይ በመመስረት የሚመለከት እና ፍልስፍናውም የሰው ልጆች የተፈጥሮ ፀጋ ያደላቸው ዋጋ እና ይህን እውን የማድረግ አቅም የሚመጣው በአመክንዮ በሚገዛ ሕይወት ስንመራና የትኛውንም ሃይማኖታዊ እምነት ስንተው ነው የሚል ፍልስፍናዊ ሃይማኖት ነው፡፡
የሰብአዊነት ጥንተ ታሪክ አጭር ዳሰሳ
መፅሐፍ ቅዱስ
አዲስ ስም እየወጣለት እየተገለባበጠ ቢቀርብልንም የሰብአዊነት ዶግማ ከሰው ልጅ ውድቀት ጋር እና ከሰይጣን የአመፅ ትምህርት ጋር የተቆራኘ ጥንታዊ ክስተት ነው፡፡ (ዘፍጥረት ምእራፍ 3) የሰው ልጅ ውድቀቱ ዋነኛ መንስኤው እንደ እግዚአብሔር መሆን እችላለው የሚል የተሳሳተ ሃሳብ ነው (ዘፍጥረት 3፣5)፡፡ የሰብአውያን ፍልስፍናና ሃይማኖት አዲስ የዘመናዊ ስልጣኔ ፍሬ ሳይሆን ከሰው ልጅ አፈጣጠር የሚቆጠር እኩል እድሜ ያለው ነው፡፡ የሰብአዊነት ፍልስፍና ዘፍጥረጥ 3፣ 4-5 ባለው የእባቡ ምክር ሊጠቃለል የሚችል ነው፡- “እባቡም ለሴቲቱ አላት፡- ሞትን አትሞቱም፣ ከእርስዋ [እግዚአብሔርከከለከላት ዛፍ ፍሬ] በበላችሁ ቀን ዓይኖቻችሁ እንዲከፈቱ እንደ እግዚአብሔርም መልካሙንና ክፉን የምታውቁ እንድትሆኑ እግዚአብሔር ስለሚያውቅ ነው እንጂ፡፡” ይህን የአመፅ አስተሳሰብ የሰው ልጅ ዳግም ያነሳው በሰብአውያን አይነቱ ፍልስፍና ነው፡፡ በዚህ መፅሃፍ በተደጋጋሚ ይህን አስተምህሮ የሚያነሱ አምልኮዎችን ዳሰናል፣ ይህ አሁን በፍልስፍና ስም መሸፋፈኑ ነው አደገኛ የሚያረገው፡፡
ጥንታውያን የግሪክ እና ሮማ ሰብአውያን
ሰብአዊነት የሚለው መገለጫ እስከ መካከለኛው ዘመን (medival /middle age) የነበረው የአውሮፓ የሰብአውያን ዳግም ልደት (European Renaissance Humanism) ድረስ ይፋዊ በሆነ መንገድ ባይታወቅም ይህ ፍልስፍና በጥንታዊ የግሪክና ሮማ ስልጣኔዎች ይንፀባረቅ ነበር፡፡ በጥንታዊትዋ ግሪክ ይህን አይነት አስተሳሰብ ከነበሩ ፈላስፎች መካከል ለመጀመርያ ግዜ ያነሳው ፕሮታጎራስ (Protagoras 490 ዓ.ዓ – 420 ዓ.ዓ) የተባለው ነው፡፡ ይህ ፈላስፋ ከሚታወቅባቸው ጥቅሶቹ አንዱ “የሁሉም ነገር መለክያ የሰው ልጅ ነው” የሚለው ይገኝበታል፡፡ ይህ አባባሉ በጥንታውያን ፈላስፎች መሃከል ከፍተኛ ውዝግብ ያስነሳ እና በወቅቱ ይንፀባረቅ ከነበሩት ዶክትሪኖች አንፃር ማለትም ጠፈር (ዩኒቨርስ) የሚለካው ወይም የተመሰረተው ከሰው ልጅ ተፅእኖ ውጭ በሆነና የራሱ ግብ ባለው ነገር ላይ ነው የሚለውን ለመጀመርያ ግዜ የተቀናቀነ አብዮታዊ አባባል ነው ማለት ይቻላል፡፡  ፕሮታጎራስ በ5ኛው ዓመተ ዓለም የነበረ እራሱን የግብረገብ (መልካም ስነምግባር) አስተማሪ አድርጎ የሚቆጥር ሰው ነበር፡፡
ሌላኛው ዲሞቅሪጠስ (Democritos 460 ዓ.ዓ- 370 ዓ.ዓ) ይህ ፈላስፋ በ19ኛው ክ/ዘመን ለመጣው የአተም ንድፈ ሃሳብ አስቀድሞ የጠቆመ ብዙዎች የዘመናዊ ሳይንስ አባት የሚሉት ፈላስፋ ከአመክንዮም ፈንገጥ በማለት ለሁሉም ነገር ምክንያት የሆነ ዓላማ (purpose)፣ አስጀማሪ (prime mover) ወይም የመጨረሻ መንስኤ (final cause) አለ የሚል ሲሆን ሁሉንም ነገር አቻዎቹ ያደርጉት እንደነበረው:- “ከቁሳዊ ምክንያት በላይ ይህ ክስተት ምን ዓላማ ነበረው?” ብሎ ሳይሆን የሚጠይቀው:- “ይህን ክስተት ምን ቀድሞት ቢመጣ ነው ሊከሰት የቻለው?” የሚለውን ብቻ ያሰላ ነበር፡፡ ልክ እንዳስተማሪው ሉሲፐስ(Leucippus 5ኛው ዓ.ዓ አካባቢ) የለየለት ቁሳዊ (materialist) እና ሁሉም ቀድሞ የተወሰነ ነው (determinist) የሚለውን እምነት ይከተል ነበር፡፡ ሁሉንም ተፈጥሮ ቁሳዊ ብቻ አድርጎ የሚቆጥር እንደመሆኑ ለመንፈሳዊ ነገሮች ምንም ቦታ የለውም ነበር፡፡
አፌቆሮስ (Epicurus 341 ዓ.ዓ- 270 ዓ.ዓ) ሌላኛው ሰብአዊ ሲሆን ዋና አላማው ፍልስፍና የሰው ልጅ ደስታና የተረጋጋ ሂወት፣ ከጭንቀት የፀዳ፣ ሰላማዊና ፍርሀት የሌለበት፣ እና ምንም የስቃይ ስሜት የማይኖርበት ለራስ በቂ ሁኖ በጓደኞች ተከቦ ሂወትን እንዲመራ ማስቻል መሆኑን ያስተምራል፡፡ የመልካምና ክፉ መመዘኛዎች የደስታ እና የስቃይ ስሜቶች ናቸው ይላል፣ ሞትም የስጋና የነብስ መጨረሻ ስለሆነ መፈራት የለበትም፣ አማልክት ሰዎችን አይሸልሙም ወይም አይቀጡም፣ ጠፈር መጨረሻ የሌለውና ዘልአለማዊ እንደሆነና በዓለም ላይ ያሉት ክስተቶች በባዶ ቦታ ላይ አተሞች በሚያደርጉት ጉዞ ላይ የሚፈጥሩት መስተጋብር ውጤት ነው በማለት ያስተምር ነበር፡፡ ከነዚህም በላይ በተመሳሳይ ሰውን ማእከል ያደረጉ ፍልስፍናዎችን ያራመዱ ብዙ ስመ ጥር የግሪክ ፈላስፎች ቢኖሩም የአርስቶትል (384 ዓ.ዓ – 322 ዓ.ዓ) እና አፍላጦን/ ፕላቶ (424/423ዓ.ዓ – 348/347ዓ.ዓ), ግን እስከ ዛሬም ድረስ የዘመናዊው ዓለም ሃይማኖታዊ እና ምድራዊ ዶግማዎች ላይ ተፅእኖ በማሳደር የምእራቡን ዓለም የዛሬውን ቅርፅ ያስያዙ ሰዎች ናቸው፡፡ ይህ ፍልስፍና በግሪክ አለም ለአንደበተ ርቱእነት የሚነበነብ ሳይሆን በተግባራዊው የፖለቲካ ዓለም ላይም ይንፀባረቅ የነበረ ነው፡፡ ለምሳሌ በ431 ዓ.ዓ. ከፔሎፖነሽያን ጦርነት በኋላ ሕይወታቸውን ላጡ የሰራዊት አባላት የሕሊና ፀሎት ንግግር በሚያደርግበት ወቅት ታዋቂው የግሪክ መሪ እና ጀነራል ፔርስለስ (Perciles) (495 ዓ.ዓ – 429 ዓ.ዓ)ስለ ቀጣይ ሂወታቸው ያለው ነገር አልነበረውም፡፡
ሮማም የድርሻዋን ሰብአውያንን አበርክታለች፡፡ ሮማዊው ገጣሚ ሉክርትየስ (Lucretius – 98? ዓ.ዓ  – 55 ዓ.ዓ) ሃሳቦቹ የኤፌቆሮስ ቁሳዊነት ይንፀባረቅባቸዋል፡፡ ሉክርትየስ ሰዎች የማይቀረውን ሞት እና አማልክትን ከመፍራት ነፃ ባለመውጣታቸው ሰላም የሌለው ሕይወት እየኖሩ ይገኛሉ ይላል፡፡ ሁሉንም ነገር ቁስ በሆኑት አተሞች ባዶ ቦታ ላይ በሚፈጥሩት መስተጋብር የሚያስከትሉት መሆኑን ማስረዳት ይቻላል ይላል፡፡ ሉክርትየስ ከሚታወቅበት ጥቅሱ አንዱ፡- “ሁሉም ሃይማኖቶች በእኩልነት ለመሃይማኑ ሚስጥራት ሲሆኑ፣ ለፖለቲከኞች ደግሞ ጠቃሚ፣ ለፈላስፎች አስቂኝ ናቸው፡፡” የሚለው ይገኝበታል፡፡ ልክ እንደ ኢፒኩረስ ሰማያዊ ሐይሎች በሰው ልጅ ጉዳይ ድርሻ (ከሞትም በኋላ) የላቸውም ይላል፡፡
ሌላው የሮማ ሰው ኦቪድ (Ovid 43 ዓ.ዓ – 17/18 ዓ.ም) ነው፡፡ ኦቪድ አማልክት ሰዎች ሌላ አላማቸውን ለማሳካት የሚጠቀሙበት ስልት ነው ይላል፡፡ ሴንካ (Seneca -54 ዓ.ዓ- 39 ዓ.ም) በበኩሉ እንደቀደመው ገጣሚ ቁሳዊውን ብቻ በማስላት ሃይማኖት አብዝሃው እንደ እውነት አድርጎ የሚወስደው፣ አዋቂዎች ስህተት እንደሆነ የሚገነዘቡት፣ መሪዎች ደግሞ ጠቃሚ መሆኑን የሚረዱት ነው ይላል፡፡ በ14ኛው ክ/ዘመን ሰብአዊነት ዳግም በሚወለድበት ግዜ ምሁራኑ የነዚህ ፀሐፍያንን ስራ ነበር ዳግም ይፈትሹ የነበረው፡፡ ያሳደሩባቸው ተፅእኖም ከፍተኛ ነው፡፡ ሲሴሮ (Cicero 106 ዓ.ዓ – 43 ዓ.ዓ) ታዎቂው የሮም ፖለቲከኛ፣ ፈላስፋ፣ ተናጋሪ፣ ጠበቃ፣ እና ሕገ-መንግስታዊነት አራማጅ የነበረ ሰው ነው፡፡ የግሪክ ፍልስፍናን ለሮም በማስተዋወቅ የሚታወቀው ለሰብአውያን ቃሉን ከመፍጠር ጀምሮ -humanitas- ከፍተኛ ቦታ የሚሰጠው ሰው ነው፡፡ ጁልየስ ቄሳር (100ዓ.ዓ – 44ዓ.ዓ) በግልፅ የሕያውነት ዶክትሪን፣ መለኮታዊ የሆኑ ፀሎት፣ መስዋእት ማድረግ የመሳሰሉትን ይቃወም ነበር፡፡ ምንም እንኳን ሮማውያን በፍልስፍናው የግሪክን ያህል በስፋት ስመ ገናናዎችን ባያፈሩም በእጅጉ የሰብአውያን አመለካከትን ያራምዱ ነበር፡፡ ከመንፈሳዊው ይልቅ በዓለማዊው ተጠቃሚ መሆንን ያስቀድሙ ነበር፡፡ በ14ኛው ክ/ዘመን እኚህ አስተሳሰቦች ከተረሱበት ቦታ በየሂወት መስኩ ብቅ ማለት በመጀመር የማሕበረሰባዊ ሽግግር ለመፍጠር በቅተዋል፡፡ የዚህ ድንገተኛ ለውጥ ምክንያቱ ምንድን ነው?
የሰብአውያን ዳግም-ውልደት (Renaissance Humanism)
የተከበሩት የምስጥ ዝርያዎች ግንባታቸውን በኩይሳ [መኖርያቸው] ይጀምራሉ፣ ምናልባትም የሚያገባድዱት በኩይሳ ይሆናል፣ ይህ ከዓላማቸው ውጪ ሌላ የማይታያቸው ስለመሆናቸውና ስለ ብልጠታቸው የሚመሰክር ተግባራቸው ነው፡፡ ሰው ግን ከንቱና ካለቦታው የሚገኝ ፍጥረት፣ ምናልባትም እንደ ሰንጠረዥ (ቼዝ) ተጫዋች የጨዋታውን ሂደት እንጂ ፍፃሜውን የማይወድ ነው፡፡ ማን ያውቃል (በእርግጠኝነት መናገር አይቻልምና) ምናልባትም በምድር ላይ የሰው ልጅ ሊደርስበት የሚፈልገው ግቡ፣ ማለቅያ የሌለው ከግቡ የመድረሱ ሂደት ሊሆንም ይችላል፣ በሌላ አነጋገር ሊደረስበት ከተፈለገው ግብ ሳይሆን በሂወት ውስጥ ማለት ነው፣ ሊደረስበት የተፈለገው ግብማ ሁሌም በቀመር (ፎርሙላ) ሊገለፅ ይችላል በእርግጠኝነት ልክ ሁለትና ሁለት አራት ነው እንደሚለው፣ እንዲህ አይነት እርግጠኝነት ደግሞ ሂወት አይደለም፣ ክቡራን ይህማ የሞት መጀመርያ ነው፡፡ የሆነ ሁኖ ሰው እንዲህ አይነቱን የስሌት እርግጠኝነት አምርሮ ሲፈራ ነው የኖረው፣ አሁንም ቢሆን እኔም እፈራዋለው፡፡ ሌላ ምንም ሳያደርግ ሰው ስሌታዊ (ሂሳባዊ) እርግጠኝነትን ሲፈልግ የሚኖር ከሆነ፣ ውቅያኖሶችን ይሻገራል፣ በፍለጋው ሂወቱን መስዋእት ያደርጋል፣ የእውን ስኬቱን ግን፣ የምር መልሱን ማግኘት፣ እማረጋግጥላችሁ ያስጨንቀዋል (ያስፈራዋል)፡፡ ያገኘው እንደሆን ሌላ የሚፈልገው ነገር አጣለው የሚለው ይሰማዋል፡፡ ሰራተኞች ስራቸውን ሲጨርሱ ቢያንስ ክፍያቸውን ይቀበላሉ፣ ቡና ቤት ይሄዳሉ፣ ቀጥሎ ወደ ፖሊስ ጣብያ ይወሰዳሉ–ይህ ደግሞ የሳምንት ስራ ይሆናቸዋል፡፡ ሰው ግን ወዴት ይሄዳል? … የሚገርም ነው፡፡ እንዲያውም ሰው አስቂኝ ፍጥረት ነው፤ የሆነ ፌዝ ነገር ያለ ይመስላል፡፡
ፍዮዶር ዶስትየቭስኪ –Fyodor Dostoyevsky “Notes From the Underground”
በዚህ ከሚያስደንቀው ደራሲ የወሰድነው የ19ኛው ክ/ዘመን ምሁሩ የገባበትን አጣብቂኝ የሚያሳየው ረዘም ያለ ጥቅስ መውሰድ የፈለግነው ሰብአውያን መገንባት የሚፈልጉት ሰዋዊ የሆነ ፍፁም ስርአት ከንቱ ልፋታቸውን ለማሳየት ነበር፣ በቀጣይ ምእራፎች በዝርዝር የምንገባበት ሲሆን በዚህኛው ረዥም እድሜ ያለውን ታሪካቸውን እንዳስሳለን፡፡
ከሮም ውድቀት በኋላ ቀጣዮቹ 1,000 አመታት መካከለኛው/ የጨለማው ዘመን በመባል የሚታወቀው ግዜ የነበረበት ነው፡፡ ይህን ዘመን የተካውና በ14ኛው ክ/ዘመን የጀመረው የሰብአውያን ዳግም ውልደት ደግሞ ሰማያዊ ሕጎችን (በተለይም በምእራቡ የነበረውን የክርስትና እምነትን) ማጥፋት ዋና አላማ አድርጎ የተነሳ አብዮት ነበር፡፡ ቶማስ አኲናስ (Thomas Aquinas – 1225.– 1274.) የአርስቶትል ፍልስፍናዎችን በመዋስ ሃይማኖትን እና አመክንዮን ለማሰባጠር ያደረገው ጥረት ለአመክንዮ አቀንቃኞች በር የከፈተላቸው ክስተት ነበር፡፡ የሰብአውያን ፍልስፍና አስኳል የሰው ልጅ እና አመክንዮ (Reason) ናቸው፡፡ ይህ ፍልስፍና በሁሉም የሰው ልጅ የሂወት መስኮች በመግባት አሻራውን ለማሳረፍ በቅቷል፡፡ ሰዎች ለመንፈሳዊው ነገር ይሰጡት የነበረው ቦታ በምድራዊው መተካት ተጀመረ በአጭር ግዜ ውስጥም ብዙ ክስተቶች ተከናወኑ፡፡ በመቶ ዓመት ግዜ ውስጥ ብቻ ብዙ አዳዲስ ግኝቶች ተደረጉ፣ ኮሎምበስ አሜሪካን አገኘ፣ አስካሁን ድረስ የሚታወቁ የስነ ጥበብ ሰዎች ተፈጠሩ፡፡
በመግቢያው ላይ እንደገለፅነው ሰብአውያን በመለኮታዊ ኃይልም ሆነ በሃይማኖት አያምኑም፡፡ የሰው ልጅ ሕልውናውንና እሱነቱን ወይም አጠቃላይ እጣ ፈንታውን መወሰንና በራሱ ሃይል እውን ማድረግ የሚችል የፍጥረት ጌታ ነው ይላሉ፡፡ ይህንም ፍልስፍናቸው — እያንዳንዱ ፍጥረት የራሱ የሆኑ ልዩ የሚያደርጉት ተፈጥሯዊ መገለጫዎች አሉት፡፡ ተፈጥሮ ፈረሶች እንዲጋልቡ፤ ወፎች እንዲበሩ ስታደርጋቸው፤ የሰው ልጅ ብቸኛ ስጦታው ደግሞ፡- የመማር ፍላጎቱ ነው — በማለት ሊገለፅ ይችላል፡፡
የሰብአዊነትን ትክክለኛ ማንነት ለመረዳት መነሻቸውን በጨረፍታ ለመመልከት ሞክረናል አሁን ደግሞ በ14ኛው ክ/ዘመን የተከሰተውን ዳግም ውልደታቸውና የአጭር ግዜ ስኬታቸውን መንስኤ ማየት ሰብአዊነትን ለመረዳት እጅግ ይጠቅመናል፡፡ የሰብአውያን ዳግም ውልደት አዲስ ብቅ ያለ ክስተት ሳይሆን ከጥንቱ ሳይቆራረጥ በመካከለኛው ዘመን በአውሮፓ በነበረው ሁኔታ ስር ከሰደደ በኋላ የመጣ ነው፡፡ የሰብአውን ዳግም ውልደት  ክርስትና ከሚፈቅደው በላይ የሮማ ካቶሊክ ስልጣን በመያዝ ሁሉንም ከስሯ ለማድረግ ሕዝቡ ላይ በጫነችው ድንቁርና/ መሃይምነት መዘዝ ነው፡፡ ለሰብአውያን የፈጠነ ስኬት ቦታ ያመቻቸው በንጉስ እና በጳጳስ (የሮማ) ሁለቱም እራሳቸውን የክርቶስ ተወካይ እያሉ እንደመጥራታቸው በማሃላቸው በተፈጠረው የበላይነት ግጭት ነው፡፡ ከሮም ውድቀት በኋላ ስልጣኔ መልሶ እንዲያሰራራና አውሮፓ የዛሬውን ቅርፅዋን እንድትይዝ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደረገው የጀርመኑ ንጉስ ቻርለማይኔ (Charlemagne747 ዓ.ም -814 ዓ.ም) ነበር፡፡ ለዚህም “ቻርለስ ታላቁ” እና “የአውሮፓ አባት” እየተባለ እንዲጠራ አድርጎታል፡፡ እራሱን እንደ ክርስቲያን ንጉስ ስለሚቆጥርም የሮማ ካቶሊክ በመላው አውሮፓ እንድትሰለጥንም ሰፊ አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡ ሆኖም ግን ይህ የንጉሱ እና የጳጳሱ መደጋገፍ ዘላቂነት አልነበረውም ከቻርለስ በኋላ የተነሱት መሳፍንትና ነገስታት ብልሹነትና የሃይማኖቱ ሰዎችም ለጥቅም መገዛት በሁለቱ መሃከል ልዩነቶችና ግጭቶች እንዲገጠሩ አድርጓል፡፡ የዚህ ግጭት የመጨረሻው መገለጫም በሄነሬ 4(1050ዓ.ም-1106 ዓ.ም). እና በፖፕ ግሪጎሪ 7 (1020-85 ዓ.ም) መሃከል የተነሳው ግጭት ነበር፡፡
ጳጳሱ ከጎኑ የተማሩትና ሰማያዊ መብቶችን ይዞ ሲሞግትና ንጉሱን ሲያወግዝ፣ ንጉሱ በበኩሉ የቆየ ልማዳዊ ስርአትና የእውቀት አልባ ነበር፡፡ በስተመጨረሻ ጳጳሱ በማሸነፍ ውግዘቱ ይነሳለት ዘንድ ንጉሱ እንዲጾምና የጳጳሱን እግር እንዲስም በማድረግ አዋርዶታል፡፡ ከዚህ በኋላ ነገስታቱ እንድትሰለጥን በፈቀዱላት ቤተ ክርስቲያን መዋረዳቸው እንደ ቤተ ክርስቲያኗ ጠንካራ ሕግ–ሃይማኖታዊ ቀኖና ከጎናቸው የንጉሳዊ ሕግ እንደሚያስፈልጋቸው የተገነዘቡት፡፡ ከዚህ በኋላ ነው ስጋዊ ፈላስፎችና የሕግ-አዋቂዎች በቤተ መንግስት ቦታ እያገኙ የሄዱት፡፡ የዳግም ውልደት ዘመን ሰብአውያን የጥንቱን የግሪክና ሮማ ስነፅሁፍ የሚያጠኑ ተደርገው ይታሰቡ ነበር፡፡ ሰብአዊ ሲባል የክላሲካል (የጥንት ግሪክና ሮማ ስነፅሁፍ) ምሁር ወይም ተጠራጣሪ (skeptic) ወይም የፈጣሪን እና ከሞት በኋላ ሂወት መኖሩን ማወቅ አይቻልም ብሎ የሚያምን (agnostic) ወይም ነፃ-ሃሳባዊ (freethinker) የመሳሰሉትን ተደርጎ ነበር የሚወሰደው፡፡ ሌሎች ደግሞ ሰብአዊ ሲባል የአዎንታዊነት (Positivism) ተከታይ አድርገው ያስቡታል ማለትም የኦገስት ኮንት (August Comte) አስተምህሮዎች ተከታይ አድርገው፡- ኦገስት ኮንት የሰብአዊነት ሃይማኖት መስራች እንደመሆኑ ማለት ነው፡፡ በመጨረሻም ሌሎች ስለ ሰው ልጅ ተፈጥሮ የሚያጠና ለሰው ልጅ በጎ የሚያስብ መልካም ተማሪ አድርገው ይወስዱታል፡፡
የመጀመርያዎቹ ሰብአውያን በመካከለኛው (በጨለማው) ዘመን ሁሉም ምሁራን፡- ባህታውያን፣ ቀሳውስት፣ ወይም ሌሎች የቤተ ክርስትያን ሰዎች በነበሩበት ግዜ ከክርስትና በፊት የነበሩትን ፈላስፎች፣ ገጣምያን፣ ታሪክ ፀሃፊዎች፣ ጠበቆች (ሕግ አዋቂዎች) ወይም ታላላቅ ተናጋሪዎችን (orators) ስነፅሁፍ የሚያጠኑ የነበሩ ናቸው፡፡ ሰስለዚህም ከመንፈሳውያኑ ጋር ሲነፃፀሩ ሰብአውያን ይባሉ ነበር፡፡ ባጭሩ የክላሲካል ስነፅሁፍ አጥኚዎች ማለት ነበር፡፡ ይህ አዲስ-የጥንት ጥናት ቤተ ክርስትያን በሰዎች እምነት ላይ ያላትን ተፅእኖ የማላላቱ ሂደት የመጀመርያው ደረጃ ነበር፡፡ በዚህም ነው ነፃ-ሃሳባውያንም ተብለው ይጠሩ የነበረው፡፡
የኮንት አስተምህሮዎች ከላይ ካሉት ጋር የማይገናኝና አዲስ ምእራፍ የከፈተ ነው፡- ሰውን ማምለክ፣ ማግነን፣ ሰው ልጅን ማእከል ያደረገ ፍልስፍና፡፡
ሌላው ያልገለፅነው የሰብአውያን ትርጉም እና ዋናው ግን ደግሞ ብዙም ያልታወቀው እነዚህ ፈጣሪን የሚያውቁት እና የሚጠሉት ሰዎች ሰብአዊነት ነው፡፡ ሰብአዊነትን እንደመሳርያ ተጠቅመው የጥንታዊውን የአመፅ ውጊያ የሚያካሂዱት ናቸው፡፡ ከምድረ ገፅ ማንኛውንም ህጋዊ ስርአት ማጥፋት የሚሹት፡፡ ሰብአዊነትን እንደመሳርያ የሚጠቀሙበት ሰብአዊነት የመንፈሳዊውን ዓለም ክህደት በመሆኑ ነው፡፡ ሰውን ከቁሳዊ ጠፈር ማእከል (ወሳኝ/የበላይ) አድርጎ በማግነን ፈጣሪንና ፍፁም የሆነ ሕጋዊ ስርአትን መካድ ይችላሉ፡፡ እኚህ በሴጣን አምልኮ ጥቁር መአርግየደረሱት (Black Adepts in the Cult of Evil)ናቸው፡፡ ይህ የሰው ልጅ በእግዚአብሔር ያለውን እምነት ለማጥፋት የሚሰራ ረዥም እድሜ ያለው እምነት ነው፡፡ ይህ የሰው ልጅ ስስ ጅማቶችን በመኮርኮር ስሜቱን ማነቃነቅ የሚያውቅበት የአሳሳቹ ፍሬ የሆነውና እነሱ የነገሱበት አዲስ የአለም ስርአት ለማምጣት አንደኛው ግንባር ነው፡፡
ኦገስት ኮንት(August Comte)
የሰብአዊነት አስተምህሮዎችን ለመጀመርያ ግዜ ስርአት ባለው መልኩ ያቀረበው ከ1798-1857 የኖረው ፈረንሳዊው ፈላስፋ ኦገስት ኮንት ነው፡፡ ኮንት በተጨማሪም የአዎንታዊነት ፍልስፍና፣ የማሕበረተሰብ ጥናት (ሶሽዮሎጂ) በ1822፣ የስነ-ምግባር (the science of individual man) በ1852 በመፍጠር እንደ አንድ የትምህርት ዘርፍ እንዲጠኑ አድርጓል፡፡ ብዙዎች የመጀመርያው የሳይንስ ፈላስፋ ተብሎ ሊወሰድ የሚችል ሰው ነው ይሉታል፡፡ የብዙዎች ፀሃፍያን፣ ማህበራዊ ሳይንስ ተመራማሪዎችንና ፈላስፎችን አስተሳሰብ ላይ ተፅእኖ ያሳደረ ሲሆን የዩቶፕያ ማህበረሰባዊው ሰይንት ሲሞን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ኮንት የአዋንታዊነት ፍልስፍናን የመሰረተው ከፈረንሳይ አብዮት ማግስት ያየውን ማህበራዊ ቀውስ ለማረም ብሎ ነበር፡፡ (ይህ በግልፅም ኦገስት ኮንት የፈረንሳዩ አብዮት (አድማ) እራሱን አብዮቱን እስኪፈጅ ድረስ ያስከተለው እልቂት  ምክንያቱ የአዎንታዊነት መጉደል ሳይሆን የአመፅ ሴጣናዊ ባሕርያት ወይም ተፈጥሮ መሆኑን ለመቀበል ፈቃደኛ ያለመሆኑን የሚያመልክት ነው፡፡)
ኮንት በ19ኛው ክ/ዘመን አስተሳሰብ ላይ በነ ካርል ማርክስ (ጋርዮሻዊነት) እና የቅርብ ጓደኛው የሆነው እንግሊዛዊው ፈላስፋ ጆን ስትዋርት ሚል ስራዎች ላይ በመንፀባረቅ ከፍተኛ ተፅእኖውን አሳድሯል፡፡ ኮንት ለማስተዋወቅ የፈለገው “የሰው ልጅ ሃይማኖት” ብዙም ስኬት ባይኖረውም በ19ኛው ክ/ዘመን ለተነሱ ስጋዊ ሰብአውያን (secular humanists) እድገት የበኩሉን አበርክቷል፡፡ “Altruism” ማለትም “ለራስ ከሚገኝ ጥቅም በፀዳ መልኩ ለሌሎች ማሰብ” የሚለውን ቃል የፈጠረውም እርሱው ነው፡፡ ኮንት ምንም እንኳ ኢ-አማኒ ቢሆንም በራሱ እሳቤዎች በመመርኮዝ ሰዋዊ የሆነ ሃይማኖት ለመፍጠር ሞክሯል፡፡ “የክርስትያኖች ውህደት” (Ecumenicalism) አቀንቃኝ ሲሆን ይህም ለበጎ አስቦ ሳይሆን ክርስትያኖችን ለማጥፋት ካለው ጥላቻ በመነሳት የሚያቀነቅነው ነው፡፡
ስጋዊ ሰብአዊነት (Secular Humanism)
“የበራለት (enlightened) እናየሰለጠነው … የሰው ልጅ ለራሱ የሚጎዳውን፣ ቂል የሆነውን፣ እያወቀ ሆን ብሎ የሚመርጥበት ግዜ እንዳለ ለመቶኛ ግዜ ደግሜ እናገራለሁ — ይህን የሚያደርገው ዝም ብሎ ቂላቂልነትንም ቢሆን የራሱን የመምረጥ መብት እንዲኖረው ሲልና ልክ የሆነውን ነገር ብቻ የመምረጥ ግዴታ የሌለበት መሆኑን ለማረጋገጥ ሲል ያደርገዋል፡፡”
ፍዮዶር ዶስትየቭስኪ -Fyodor Dostoyevsky “Notes From the Underground”
ኦገስት ኮንት በሕይወት ዘመኑ እያለ “የሰው ልጅ ሃይማኖት” ብሎ ሞክሮት የነበረው ፍልስፍና ሂወት የዘራው በስጋዊ / ዓለማዊ ሰብአዊነት ነበር፡፡ ብዙዎች የሴራ ታሪክ አጥኚዎች ስጋዊ ሰብአዊነትን “አዲሱ ጋርዮሻዊነት” (“አዲሱ ኮሚውኒዝም”) እያሉ ይጠሩታል፡፡ በዚህ ፍልስፍና የሃገራዊ ራእይ እጦት፣ የተፈጥሯዊ ስነ ምግባር ሕጎች ጥሰት፣ ደንታ ቢስነት፣ ሴሰኝነት፣ አምባገነንነት ወዘተ. ይንፀባረቃሉ፡፡ በአሁኑ ሰአት ለሚታየው አርቆ አለማሰብ፣ የመንፈሳዊ ሕይወት ዝቅጠት፣ ሕይወትን የሃሰት የማስመሰል /የተውኔት መድረክ አድርጎ መመልከት ወይም የሕሊና ቢስ ራስ ወዳድነት በአጠቃላይ ግራ የሚያጋቡ የሂወት ዘይቤዎች ከዚሁ ፍልሰስፍና ፍሬዎች ናቸው፡፡

የሰብአውያን “ደስተኛ ሰው” የተሰኘው ዘመናዊው አርማቸው፡፡

ስጋዊ ሰብአዊነት ሃይማኖት ሲሆን፣ በእግዚአብሔርም ሆነ በየትኛውም መንፈሳዊ የሆኑ ነገሮች የማያምን፤ የሰው ልጅ ብቻ የሚመለክበት ነው፡፡ በሰብአዊነት ዙርያ በመፃፍ የምትታወቀው ክሌር ቻምበርስ (Claire Chambers)፡- የሰው ልጅ በባርነት ከመገዛቱ በፊት አስተሳሰቡ ከመንፈሳዊ ወደ ስጋዊ/ ዓለማዊ መሸጋገር አለበት፡፡ ራሱን ምንም አይነት መንፈሳዊ ግዴታ የሌለው እንስሳ እንደሆነ አድርጎ እንዲመለከት የግድ መማር ይኖርበታል፡፡ ከዚህ በኋላ የሰው ልጅ አንዴ ከእግዚአብሔር መርሖች ውጪ ከሆነ ጋርዮሻዊ ለሆኑ መርሖች ፍፁም ተገዢ ለመሆን የሚያደርገው ጉዞ ይረጋገጣል፡፡” ትላለች፡፡
የሰው ልጅ በእግዚአብሔር አምሳል ነው የተፈጠረው፤ በሌሎች ፍጥረታት ላይም ስልጣን ነበረው፡፡ (ዘፍጥረት 1፣ 28-30) የሰው ልጅ ግን እንደ እግዚአብሔር ትሆናላቹ ለሚለው የአሳሳቹ ምክር ወድቀው ስህተት ሰሩ፡፡ (ዘፍጥረት 3፣ 1-8) ቸሩ እግዚአብሔር የሰውን ልጅ ዝም ብሎ አልተወውም፡፡ አንድያ ልጁን ክርስቶስን መስዋእት በማድረግ የሰውን ልጅ የመጀመርያውን የሃጥያት ሰንሰለት በማስተሰረይ በጥሶለታል፡፡ እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ከሰጠው ትእዛዛት አንዱ በሰው ልጅ ላይ ጥቃት የሚፈፅም ሁሉ ዋጋውን እንደሚከፍል ዘፍጥረት 9፣ 6 ላይ፡- “የሰውን ደም የሚያፈስ ሁሉ ደሙ ይፈሳል፤ ሰውን በእግዚአብሔር መልክ ፈጥሮታልና፡፡” ሲል ያስጠነቅቃል፡፡ ይህም የተባለበት ምክንያት ፈጣሪ የሐጥያት ምኞቶችንና ሰው ምን ያህል ለባልንጀራው ክፉ ሊሆን እንደሚችል ስለሚያውቅ ነው፡፡ የሰው ልጅ ታሪክ እንደሚያስገነዝበን የሰው ልጅ የሰው ልጅን ከመጉዳት ወደኋላ እንዳላለ ነው፡- ታሪክ ማገላበጥ ሳያስፈልገን በዚህ የስልጣኔ ዘመን በሚባለው እንኳ ምንም ከጥንቱ የአረመኔዎች ሕይወት ብዙም እንዳልተራቀ ለመገንዘብ ከዝነኛ ዜና ማሰራጫዎች አንዱን ለሰከንድ ማየት በቂ ማስረጃ ይሆነናል፡፡ እንደምንመለከተው የሰብአውያን ፍልስፍናና ሃይማኖት አዲስ የዘመናዊ ስልጣኔ ፍሬ ሳይሆን ከሰው ልጅ አፈጣጠር የሚቆጠር እኩል እድሜ ያለው ነው፡፡ የሰብአዊነት ፍልስፍና ዘፍጥረጥ 3፣ 4-5 ባለው የእባቡ ምክር ሊጠቃለል የሚችል ነው፡- “እባቡም ለሴቲቱ አላት፡- ሞትን አትሞቱም፣ ከእርስዋ [እግዚአብሔርከከለከላት ዛፍ ፍሬ] በበላችሁ ቀን ዓይኖቻችሁ እንዲከፈቱ እንደ እግዚአብሔርም መልካሙንና ክፉን የምታውቁ እንድትሆኑ እግዚአብሔር ስለሚያውቅ ነው እንጂ፡፡” በ1933 በአሜሪካ ቀደም ካሉት ለየት ያለ ቅርፅ ይዞ ወደ መድረክ ብቅ ያለበት ግዜ ነው፡፡ በዛ ያሉ በየመስካቸው ጥሩ ስም ያተረፉ ሳይንቲስቶች፣ አስተማሪዎች፣ ሚኒስትሮች ፀሃፊዎች፣ አእንዲሁም ሌሎች ተፅእኖ አድራጊ ግለሰቦች፣ ቡድኖች እና ደጋፊዎች የሰብአውያን መግለጫ (Humanist Manifesto) ፅፈው በጋራ ፈረሙ፡፡  ይህ ሰነድ ወይም መግለጫ የስጋዊ ሰብአዊነት አንኳር ነጥቦችን የያዘ ነው፡፡ የዚህችን አጭር መግለጫ ከባድ መዘዝ ለመረዳት የተወሰኑትን ጭብጦች መዳሰስ በቂ ነው፡-
Øሰዎች ከሃይማኖት ተፅእኖ በመላቀቅ ዘመናዊው ዓለምን በሰፊው በመረዳት መሰረታዊ ለውጥ የሚያመጡበት ግዜው አሁን ነው፡፡
Øየሳይንሳዊ እና ኢኮኖሚያዊ ለውጦች የቆዩ እምነቶች እንዲረበሹ አድርገዋል፡፡
Øየሰው ልጅ እውቀትና ልምድ በፍጥነት እያደገና እየጎለበተ በመሄድ አዳዲስ ግኝቶች እንደፈጠሩ አስችሏል፡፡ ስለሆነም አለም ላይ የሚገኙ ሃይማኖቶች በሙሉ በአዲሱ የአስተምህሮ ሂደት የመመራት ግዴታ ውስጥ ገብተዋል፡፡
ከዚህ በመነሳት ይላል መግለጫው (ማኒፌስቶው) የሚከተሉት በ15 ነጥቦች የተያዙትን “እውነታዎችን” ይሰጡናል፡-
Øየመጀመርያው፡ ሃይማኖታዊ ሰብአውያን ጠፈርን (ዩኒቨርስ) በራሱ የሆነ እንጂ የተፈጠረ ነው ብለው አይቀበሉም፡፡
Øሁለተኛው፡ ሰብአዊነት የሰው ልጅ የተፈጥሮ አካልና የተገኘውም ቀጣይ የሆነ ሂደት ውጤት ነው ብሎ ያምናል፡፡
Øአራተኛው፡ ሰብአዊነት የሰው የሃይማኖታዊ ባህልና ስልጣኔው፣ አንትሮፖሎጂ [የሰው ልጅ ምንጭ፣ ማ/ሰብና ባህል ጥናት] እና ታሪክ በግልፅ እንደሚያሳዩት ከተፈጥሮአዊ አካባቢው ጋር በሚፈጥረው መስተጋብር ቀስ በቀስ የመጡ ለውጥ ናቸው፡፡ …
Øአምስተኛው፡ ከሰው ውጪ በሆነ መንገድ ምንም አይነት ሰብአዊ እሴቶች (ሕጎች/ስነምግባሮች) ሊመጡ እንደማይችሉ….
Øስድስተኛው፡ … እምነቶችና “አዳዲስ ሃሳቦች” ግዚያቸው እንዳለፈ ተረድተናል፡፡
Øሃይማኖታዊ ሰብአዊነት የሰውን ባህርያት (ፐርሰናሊቲ) ሙሉለሙሉ እውን ማድረግ (ማወቅ/መጠቀም) የሰው ልጅ ሂወት አላማ መሆኑን ይገነዘባል፣ የዚህን መበልፀግ እና እውን መሆንን ይሻል፣ እዚህና አሁን [በምድር]፡፡ የሰብአውያን ማህበራዊ ስሜታቸው ግለት ማብራርያው ይህ ነው፡፡
Øአስራ አራተኛ፡ ሰብአውያን በማያጠያይቅ ሁኔታ እንደሚያምኑት አሁን ያለው ስግብግብና ትርፍን ብቻ ማእከል ያደረገ ማህበረሰብ በቂ (ብቁ) እንዳልሆነ በራሱ አሳይቷል፤ እናም [በማህበረሰቡ አደረጃጀት] ዘዴዎች፣ ቁጥጥሮች እና ማነቃቅያዎች መለወጥ አለባቸው፡፡ የሕይወት መኖርያ ግብአቶች እኩል ይከፋፈሉ ዘንዳ ሕብረተሰባዊ እና የሕብረት ስራ አደረጃጀት ማእከል ያደረገ ኢኮኖሚያዊ ስርአት መዋቀር አለበት፡፡ የሰብአዊነት ግብ ሰዎች በፈቃዳቸው ለጋራ ጥቅም የሚተባበሩበት ነፃ እና ሁሉን አቀፍ ሕብረተሰብ ማምጣት ነው፡፡ ሰብአውያን በጋራ ዓለም የጋራ ሂወትን ይጠይቃሉ፡፡
ሌሎቹም ነጥቦች እነዚህን የመሳሰሉ ጋርዮሻዊነትንና ኢ-አማኝነትን የሚሰብኩ መፈክሮች ናቸው፡፡ ከላይ ያነበብናቸው ነጥቦች የጋርዮሻውያን፣ የአዝጋሚ ለውጥ አቀንቃኞች (ኢቮሊሽኒስቶች)፣ እና ኢ-አማንያን መርሖዎችን አጠቃሎ የያዘ ሃሳብ ነው፡፡ ካርል ማርክስም ጋርዮሻዊነትንና ሰብአዊነትን አንድ አድርጎ ነበር የሚወስዳቸው፡፡ አስራአራተኛው ነጥብ ነፃ-ገበያ እንደወደቀና ጋርዮሻዊነት መተከል እንዳለበት የሚያሳይ ነው፡- ነጥቦቹ ከተፃፉ ቀጥለው በመጡት አምስትና ስድስት አስርት አመታት ከተከሰቱት እውነታዎች ዓለም እንደተረዳው ማሕበረሰባዊነትና ጋርዮሻዊነት ርእዮተ አለም በገባባቸው ሃገሮች ሕዝቦችና ኢኮኖሚያቸውን አሽመድምዶ ብዙዎችን ከበላ በኋላ ፍርክስክሱ መውጣቱን ነው፡፡ በዚህ መግለጫ ላይ ፊርማቸውን ካኖሩት ውስጥ ገንኖ የሚወጣው ጆን ዴዊ ይገኝበታል፡፡ “የተራማጅ ትምህርት” (“progressive education”) ቀራጩ ዴዊ በአሜሪካ ትምህርት ዘርፍ ላይ ከፍተኛ ተፅእኖ እንዲፈጥሩ የሚስጥር ማህበሩ እጅ (የየል ዩኒቨርስቲው ስከልና ቦንስ እና የክፌለር ፋውዴሽን) ከተፈጠሩት፣ ከተደጎሙትና ወንበር ከተሠጡት ሰዎች ቁንጮው ነው፡፡ ይህ በሌላ መፀሃፋችን የተመለከትነው ጉዳይ ሲሆን ባጭሩ እዚህ ላይ ስለ ዴዊ የትምህርት እሴት እና ሰብአዊነት ትስስር ትንሽ እንላለን፡፡

ሳተርደይ ሪቪው 50 ዓመቱን (1924-1974) በሚያከብርበት ግዜ ለአንባቢዎቹ አንድ ጥያቄ አቅርቦ ነበር፡- ላለፉት ሃምሳ ዓመታት ከየዘርፉ ትልቅ ተፅእኖ የፈጠሩት ማናቸው የሚል፡፡ በዚህም መሰረት በትምህርት ዘርፍ የተመረጠው ጆን ዴዊ ነበር፡፡ በዚህ ወሳኝ ቦታ ላይ ትልቅ ሚዛን የያዘ ሰው አስተሳሰብ ምን ያህል ፋይዳ እንደሚኖረው መገመት አይከብድም፡፡ ሰብአዊው ዴዊ ስለ እግዚአብሔር እና ሃይማኖት ያለውን አመለካከት ባጭሩ እንደሚከተለው ይገልፀዋል፡- “እግዚአብሔርም ሆነ ነብስ [መንፈስ] የሚባል ነገር የለም፡፡ በመሆኑም ግዜው ላለፈበት ሃይማኖት ምንም አይነት እምነት አያስፈልግም፡፡ ቀኖና እና ሃይማኖት ያስወገድናቸው እለት፣ የማይሻር እውነት የሚባለው አብሮ ይወገዳል፡፡ በመሆኑም የማይሻረው ሕግ ወይም ቋሚ የሆኑ ፍፁም መርሆች (permanent absolutes) ምንም ዓይነት ቦታ አይኖራቸውም፡፡” ይህን አይነቱ አስተሳሰብ በጋርዮሻዊው ሌኒን ንግግሮች ይገኙበታል፡፡ ሌኒን ስለ ግብረገብ (ሞራል) ሲያብራራ “አዎ! በእርግጥ እኛ በእግዚአብሔር አናምንም፤ ዘልአለማዊ በሆነ ሞራልም አናምንም፡፡ … አሮጌውና ጨቋኝ የአገዛዝ ስርአት ድምጥማጡ ለማጥፋት እና የወዛደሩን ሕብረት ለመፍጠር ለምናደርገው ጥረት የሚያስፈልጉን ማናቸውም ነገር ሞራላዊ ናቸው፡፡” አውዳሚው ሌኒን የሰው ልጅ የሞራል ስረ መሰረቱ ሃይማኖት መሆኑን በሚገባ ያውቅ ነበር፡፡ ለዚህም ነው ሌኒን የሚከተለውን የሚዘፍነው፡- “ሃይማኖት ላይ ጥቃት መፈፀም ይኖርብናል፡፡ ሃይማኖት ይውደም! ረዥም እድሜ ለኢ-አማኝነት፡፡ የኢ-አማኝነት መስፋፋት ዋነኛ የቤት ስራችን ይሆናል፡፡ በመሆኑም፣ ዘለአለማዊ እውነት በጋርዮሻዊነት ፍፃሜውን ያገኛል፡፡ ሁሉም ሃይማኖቶችና የስነ ምግባር እሴቶች በጋርዮሻዊነት ይጠፋሉ፡፡” ባጭሩ ስጋዊ ሰብአዊነት (ወይም ሰብአዊነት) የተቀመረው በኢ-አማንያን፣ በጋርዮሻውያን እና በአዝጋሚ ለውጥ (ኢቮሉሽኒስት) ተከታዮች መርሖዎች ነው፡፡ ከዚህ ከመጀመርያው መግለጫቸው ብዙም ለውጥ የሌለበት ሌሎች መግለጫዎችን ያሳተሙ ሲሆን ክህደታቸው እየጨመረ እንደመጣ (ከዚህ በላይ ከተቻለ ማለት ነው) የሚያሳዩ እንጂ ብዙም ለውጥ የለባቸውም፡፡ ሁለተኛው የሰብአውያን መግለጫ (Humanist Manifesto II) ከአንደኛው መግለጫ ከ40 ዓመታት በኋላ 1973 ነበር የተለቀቀው፡፡ በግልፅ ከመጀመርያው ላይ የጨመረው ነገር ቢኖር የሉላዊ ማሕበረሰብ ግንባታ፣ ዓለም አቀፋዊ የሕግ ስርአት እና አገር-ዘለል ፌደራል መንግስት (Transnational federal government) የመሰለ የዓለም ስርአት ግንባታ የሚል የአዲስ የዓለም ስርአት የሰብአውያን ጥሪ ይገኛል፡፡ ይህ ጥሪ የሚስጥር ማህበራቱ የመጨረሻ ግባቸው መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ለዚህም ነው ይህን እውን ለማድረግ እየሰሩ ባሉ ዓለም አቀፍ ተቋማት ውስጥ ሰብአውያን ቁልፍ ሚና የሚጫወቱት ለመጥቀስ ያክል፡- የመጀመርያው የዩኔስኮ ዳይሬክተር ጁልያን ሃክስሌ፣ የመጀመርያው የዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር ብሮክ ኪስሆልም፣ የመጀመርያው የዓለም እርሻና ምግብ ድርጅት ዳይሬክተር ጆን ቦዊድ ከብዙዎቹ መሃከል ሊጠቀሱ የሚችሉ ሰብአውያን ናቸው፡፡

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s