ቅንጫቢ ፭ የሽብር ውሎው ትንተና ወይም ፍልስፍና (ካልታተመ መፅሃፍ የተወሰደ በግደይ ገ/ኪዳን እና ተክሉ አስኳሉ)

Posted: March 7, 2012 in ሽብር
13
የሽብርውሎው ትንተና
በዚህ ምእራፍ አሁን የአሜሪካን ፖለቲካ የተቆጣጠሩት ቁንጮ ጥቂቶች ይህን የሽብር ዘመቻቸውን የሚያካሂዱበት መንስኤ እምነታቸው ነው ብለን የተቀበልነውን ትንተና እንዳስሳለን፡፡ የመጀመርያ ክፍል ርእስ ገፅ ላይ የፃፍነው የአሌክሳደር ሶልዘንትሲን ጥቅስ ርእዮተ አለም ክፋት የሚፈልገውን ሰበብ እንደሚሰጥ አሳይቶና፡፡ አሁን አለምን በማሸበር ለመግዛት እየጣሩ ያሉት ምን አይነት ርእዮተ አለም እንደሚከተሉና ያመጣጥ ታሪኩን እናያለን፡፡

ከሰላም ጦርነት የሚመርጡት
ራሳቸውን ኒዮ-ኮንዘርቫቲቭ /አዲሶቹ-ወግ አጥባቂዎች እያሉ የሚጠሩት ፋሺስቶች፣ ስያሜያቸው ከህዝብ መቅረብያ ጭምብል የሆናቸው ምንም ወግ ወይም ሰብአዊነት የሌላቸው የፅንፈኞች ስብስብ ናቸው፡፡ ዌብስተር ታርፕለይ፡ 9/11 Synthetic Terror Made in USA በሚለው መፅሃፉ አዲሶቹ ወግ አጥባቂዎች ለራሳቸው ብቻ በሚነጋገሩት የሚስጥር ዶክትሪናቸው(esoteric doctrine) እና ህዝቡ እንዲሳብ የሚነግሩት ዶክትሪን (exoteric doctrine) መሃከል መለያየት መቻል አለብን ይላል፡፡ የሚስጥር ዶክትሪናቸው በፅሁፍ ሳይሆን በቃል የሚተላለፍ ነው፡፡ ቢሆንም ግን አንዳንድ ህትመቶቻቸው መሰረታዊ ሃሳባቸውን እንድንረዳ ያግዘናል፡፡ ከዚህም የጦርነት፣ የአመፃ፣ የጥላቻ፣ የመፈንቅለ መንግስት፣ የአስቸኳይ ግዜ ወታደራዊ አገዛዝ(martial law)፣ እና በተለይም ደግሞ የሽብር ጥሪን ሲያደርጉ ነው የምናገኛቸው፡፡ በአሜሪካ የአዲሶቹ ወግ አጥባቂዎች አባት ከሆነው ሊዮ ስትራውስ /Leo Strauss(1899-1973) ፅሁፎች ትንሽ ማጣቀስ ርእዮተ አለማቸውን እንድናውቅና ተግባራቸውን እንድንረዳ ያግዘናል፡፡ የመጀመርያው የአዲሶቹ ወግ አጥባቂዎች ትውልድ የትሮትስኪያዊ ኮሚኒዝምን ለምሳሌ የተፎካካሪ ቁንጮዎች (competing elites)የሚለው የትሮትስኪ ንድፈ ሃሳብ መስመርን የሚከተሉ ሲሆኑ ከሁሉም በላይ በልል/ሊበራል ቁንጮዎችና በራሳቸው መሃል ያለውን ግጭት ለፖለቲካው ሂደት ማእከል አድርገው ይቆጥራሉ፡፡ ሊዮ ስትራውስ ስለሽብር አስፈላጊነት በግልፅ ይሰብካል፡፡ ሲበዛ ሰላም፣ ስልጣኔና ብልፅግና የሰው ልጅን መሰረታዊ ተፈጥሮ የሚያበላሽ ነው ይላል፡-
ለዘመናት ሰዎች ሳይታወቃቸው ወደ ሰላማዊ አንድ አይነት ዓለም (homogeneous state) ላይ ለመድረስ መቼም የተስፋቸውን ሳያገኟት ማለቅያ የሌለው ልፋትና ስቃይ አሳልፈዋል፣ ልክ ከፈለጉበት ሲደርሱ ደሞ ሰብአዊ ተፈጥሯቸውን እንዳጠፉ ይረዳሉ፣ እናም እንደ ዑደት ወደነበሩበት ከሰብአዊነት በፊት ወደነበረው የታሪክ መጀመርያ ይመለሳሉ፡፡ (Leo Strauss and Alexandre Kojève, On Tyranny, 209)
ሰዋች ሰላም የሰፈነበት ዓለም ላይ ደርሰው ተፈጥሯቸው ከመጥፋቱ ሲረዱ ምንድነው የሚያደርጉት፣ ምንድነው ታሪክን እንደገና ከመጀመርያ እንዲደግሙ የሚያደርጋቸው? ይቀጥልና፡-
…ፀሃይና የሰው ልጅ ሰውን መተካታቸውን እስካላቆሙ ድረስ፣ የሰው ልጅ ተፈጥሮ ሙሉለሙሉ እስጋልተበገረ ድረስ፣ በዚህ ተስፋ መቁረጥ አያስፈልግም፡፡ ሁሌም ቢሆን ታላቅ ጀብዶ ወይም ክቡር ስራ ለመፈፀም የማይመች ወይም የሰው ተፈጥሮን አጥፊ በሆነ መንግስት ላይ የሚያምፁ ሰዎች ይኖራሉ፡፡ (Strauss, 209)
እነዚህ እውነተኛ ጀግኖች ሰላምና ብልፅግና በበዛበት ዓለም ላይ ሲያምፁ ምን ተግባር ነው የሚከተሉት? ለዚህም የጥፋት መልሱን ይሰጣል፡-
…ምንም ዓይነት አዎንታዊ ግብ ወደሌለው የተቃውሞ እንቅስቃሴ፣ ሁሉን ተቃዋሚ/ አጥፊ ወደሆነ (nihilistic negation) መስመር፣ ሊገቡ ይችላሉ፡፡ ምናልባት የከሰረ መንገድ ቢሆንም ሁሉን-አጥፊ (ኒሂሊስት) የሆነ አብዮት በሁሉን አቀፍና አንድ ዓይነት ሰላማዊ መንግስት (ዓለም) ስር ብቸኛው ክቡርና ታላቅ ምግባር ነው የሚሆነው፡፡ ማንም ግን ስለ ስኬታማነቱ ወይም ክሽፈቱ ማወቅ የሚችል የለም፡፡ (Strauss, 209)
ሁሉን አጥፊ ተቃውሞ ከሚባለው ምን መረዳት ይቻላል? በ19ኛው ክ/ዘመን የሁሉን አጥፊ ርእዮተ ዓለም (nihilism) የሽብር ርእዮተ ዓለም ነበር፡፡ ባለስልጣናትን ሲገድሉ የነበሩት ፈንጅ ወርዋሪዎቹ ኢ-አማንያን፣ ስርአት-አልበኞች (አናርኪስት) እና ሁሉን አጠፊ (ኒሂሊስት) ነበሩ፡፡ በ20ኛው ክ/ዘመን የኒሂሊስቶች አብዮት በጣም ፅንፈኛ ከሆኑት የፋሺስትና ናዚ ክንፎች ጋር የተያያዘ ነበር፡፡ “ሞት ለዘላለም ይኑር!” መፈክራቸው ነበር፡፡ ስትራውስ እንዲህ በመፃፍ ለፋሺስታዊነት፣ ለነብሰ ግድያ፣ ለብጥብጥ፣ ለጦርነት፣ ለዘር ማጥፋት፣ በተለይም ደሞ ለሽብር በር ከፋች ሁኗል፡፡ ይህንንም በፅሁፍ ለማመን አላፈረም ይለናል ከላይ ያጣቀስነው የዌብስተር ታርፕለይ መፅሃፍ፡፡ ታርፕለይ ሊዮ ስትራውስ የሰውን ዘር ወደ ድንጋይ ዘመን በነበረበት ግዜ፣ 10,000 ዓመተ ወደኋላ፣ ለመመለስ ነው እየፈለገ ያለው ይላል፤ እዚህጋር ስትራውስ ከድንጋይ ዘመን ጋር ፍቅር ከነበረው የፈረንሳይ አብዮት የወለደው የሽብር ያገዘዝ ዘመን ላይ ተፅእኖ ከነበረው ከፈላስፋው ሩሶ ጋር አንድ የሚያደርጋቸው ነጥብ ነው ይላል ፅሁፎቹን በማጣቀስ፡፡ ወደ ድንጋይ ዘመን የሚመለሱትን ሲያፅናናም፣ ስትራውስ፡-
ማቆምያ የሌለው ኢ-ሰብአዊ መጨረሻ ውስጥ ከመግባት፣ እንዲህ ያለ የሂደቱ መደጋገም – ለሰውና ለሰው ልጆች የሂወት አዲስ ኪራይ /ሊዝ/ – ተመራጭ አይሆንም? ምንም’ኳ የወቅቶች ዑደትን አውቀን ክረምት ዳግም እንደሚመጣ እየተገነዘብን እያንዳንዷን የፀደይ ወቅትን አንደሰትባትም?(Strauss, 209)
ለሊዮ ስትራውስ ወደ አሰቃቂው ድንጋይ ዘመን መመለስ እንደ ፀደይ ነው የሚቆጥረው፡፡ ወደ ድንጋይ ዘመን ከመመለስ ይልቅ ግን ለሰው ልጆች ተፈጥሮ አማራጭ ማስተንፈሻ ጀብዶ ወይም ክቡር ምግባር ጓደኛው አሌክሳደር ኮጄቭ የሚያቀርበውን አማራጭ ያጣጥለዋል፡ “ኮጄቭ ሰላም በሰፈነበት ዓለም አማራጭ ማስተንፈሻ ያገኘ ይመስላል፡፡ ለፖለቲካዊ አመራር በሚደረግ ትግል ውስጥ የሞት ስጋት የያዘ አደጋን የተገኘ ይመስላል፡፡ …ግን እንዲያ ያለ ጀብዶ ለጥቂት አናሳዎች ብቻ የሚደርስ አማራጭ ነው፡፡ ደሞም ይህ አስቀያሚ አማራጭ አይደለምን፡- የሰው ተፈጥሮ የመጨረሻው መጠበቅያ/ማቀብያ የፖለቲካዊ ግድያ ስጋት ብቻ የሆነበት፣ ለዛውም በጣም በሚያስጠላ የቤተ መንግስት አብዮት ውስጥ የሚገኝ? እንዲህ ያለ ትንሽዬ አመፃ የሰው ተፈጥሮን ከመበላሸት ለመታደግ ለስትራውስ በቂ አይደለም፡፡
ማርክስና ኢንግልስ ከላቀ የኢኮኖሚያዊ እድገት ደረጃ ስለሚመጣ የጋርዮሻውያን ዩቶፕያ የሚያስገኘውን የነፃነት ዘመን ፅፈው ነበር፡፡ ስትራውስ ይህ የጋርዮሻዊ መፈክራቸውን ወስዶ በመሃከለኛው መደብ እሴቶችና የብልፅግና ጉዞዎች ላይ የበቀል እርምጃ መውሰጃ ያደርገዋል፡- “የሚመጣውን “የነፃነት አድማስን” –‘realm of  freedom’–ለመቋቋም፣ ካሁኑ ግዜ እያለ፣ የሁሉም ሃገሮች ጦረኞችና ሰራተኞች ተባበሩ፡፡ ባላችሁ አቅም፣ መከላከል ካስፈለገው፣ “የመሰረታዊውን አድማስ” — ‘realm of necessity’ተከላከሉ፡፡” ይላል፡፡ ስትራውስ እያለ ያለው ሰላም፣ ስልጣኔና ብልፅግና ለአገዛዝ የማይሆን በመሆኑ ለማጥፋት ማንኛውም ነገር መደረግ አለበት ነው፡፡ በግልፅ እንዲህ ብለው ለመፃፍ ከደፈሩ በሚስጥር ደግሞ የያዙት ምን ሊሆን ነው? የአዲሶቹ ወግ አጥባቂዎች ፍልስፍና ከሊዮ ስትራውስ በተጨማሪ የናዚ ፍልስፍና ፈርቀዳጅ ከሆነው የጀርመን ፈላስፋ ኒቼ (Nietzsche) ይገኛል፡፡ በተጨማሪም የናዚ አባል የሆነው ካርል ሽሚት(Carl Schmitt) እና ማርቲን ሄድገር (Martin Heidegger)ዋናዎቹ ናቸው፡፡ የአዲሶቹ ወግ አጥባቂዎች የስልጣኔ ትሩፋቶች አለመፈለግን ለመረዳት ለተራው ሰው እጅግ ስለሚከብድ ማብራራቱ አስፈላጊ ነው የሚሆነው፡፡ በኒው ዮርክ ሲቲ ዩኒቨርሲቲ ብሮክሊን ኮሌጅ የፖለቲካዊ ሳይንስ ረ/ፕሮፌሰር የሆነው ኮሬ ሮቢን (Corey Robin) ዋሽንግተን ፖስት ጋዜጣ ላይ በግንቦት2004ያወጣው ፅሁፍ ነበር፡፡ ፅሁፉ ከ9/11 ጥቃት በፊት በ2011 ከታዋቂ ወግ አጥባቂዎች ጋር ያደረገውን ቃለ ምልልስ ዳሰሳ ነበር፡፡
ሮቢን ከኢርቪንግ ክሪስቶል(Irving Kristol)፣የጦርነት ሰባቂው Project for a New American Century ተቋም ዋናው ሰው፣ በክሊንትን አስተዳደር ግዜ ከኢራቅ ጋር ጦርነት እንዲደረግ ሲወተውት የነበረው ዊልያም ክሪስቶል(William Kristol)አባት፣ አሜሪካ ኢኮኖሚያዊ እድገት ላይ ብቻ ማተኮሯ እጅግ እንደሚያስቆጭና ሉላዊ የበላይነቷን ለመከላከል ብዙ እንዳልሰራች እንዳሳዘነው ተናግሯል፡፡ ሮቢን “ወግ አጥባቂዎቹ ከልማት ስሌትና ቴክኖሎጂ ይልቅ ሚስጥራቱና ወኔ” እንደሚበልጥባቸው “mystery and vitality over calculation and technology”ከገንዘብና ገበያም በላይ ሚስጥራትና ወኔ እንደሚበልጥባቸው ፅፏል፡፡አሜሪካን ወደ ኢራቅ ጦርነት ካስገቡት አንዱ የሆነው ልዊስ ሊቢ (Lewis I. “Scooter” Libby)ይሄ የሰላምና የብልፅግና አምልኮ በፕ/ት ክሊንተን ደካማ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ተንፀባረቋል፣ ይህ ቢን ላደን እንዳሻው እንዲፈነጭ ፈቅዶለታል በማለት ያማርራል፡፡ ሮቢን በመቀጠል ምንም እንኳ ወግ አጥባቂዎቹ ሃብትና ብልፅግና፣ ህግና ስርአት፣ መረጋጋትና ቅደምተከተል የሚያከብሩ ቢሆኑም ክሊንተን እነዚህን ሲከተል ይወቅሱታል ይላል፡፡ የክሊንተን ብልፅግናን መሻት ጥልቀቱንና ፖለቲካዊ ትርጉሙን ያጣ ማህበረሰብ እብዲፈጠር አድርጓል ይላሉ፡፡ በተጨማሪም ክሊንተን የሚታየው የማይረባ የዓለም ስርአት ከዚህ ጭለማና ክፉ አለምን ለመቋቋም የሚያስፈልገውን ወግ አጥባቂዎቹ ተራ/አሰልቺ የሆኑት ሰላምና ብልፅግና በላይ የሚመርጡትን አረመኔያዊ ፅናትና ብቃት (virtù) ይጎለዋል ይሉታል፡፡
ወግ አጥባቂዎቹ ይላል ሮቢን 9/11ን ከሚያደነዝዘው የብልፅግና ፖለቲካ በላይ የሚመርጧቸውን እንደ ጀግንነትና ትግል ያሉ ፖለቲካዊ እሴቶቻቸውን የሚያሳዩበት ጥሩ አጋጣሚ አድርገው ነው የሚቆጥሩት፡፡ ምክንያቱም9/11 ወደ ህዝቡ በመሄድ ስለ እጣ ፈንታና መስዋእትነት መለፈፍ የሚያስችላቸውን አጋጣሚ ፈጥሮላቸዋል፡፡ (Washington Post, May 2, 2004)
ፖለቲካዊ ተንታኙ አጋጣሚ ቢለውም እኛ ግን ለዚሁ ልፈፋቸው ሲሉ 9/11 እውን እንዲሆን ያወረዱት መዓት እንደሆነ እንገነዘባለን፡፡ ካቶሊኩ ፓትሪክ ቡካናን(Catholic traditionalist Patrick Buchanan) በ1999-2000 ላይ በነበረው የምርጫ ዘመቻ ወቅት በወግ አጥባቂዎቹ ሲንፀባረቅ የነበረው አዲስ ግጭት ፍለጋቸው እንዳሳሰበው ገልፆ ነበር፡፡ ጆርጅ ቡሽን የከበቡት አዲሶቹ-ወግ አጥባቂዎች ብዛት ገርሞት ነበር፡፡ ሲሰብኩ የነበረው ዩ.ኤስ. እንደ ሉላዊ የበጎ ምግባር ሃይል አድርጎ ለመቅረፅ የሚደረገው ጥረትም አስደምሞታል፡፡ እነዚህ ጆርጅ ቡሽን የከበቡት የወግ አጥባቂዎቹ ስብስብ ስብስባቸውን ቩልካን እያሉ ነበር የሚጠሩት፡፡ ቩልካን ወይም ሄፋስቶስ ደግሞ በግሪክ-ሮማ አማልክት ስያሜ መሰረት የእሳተ ጎመራ፣ የብረት ቀጥቃጮችና የእሳት አምላክ ነው፡፡ ይህ በቀላሉ የሚታይ ያናሳዎች ስብስብ አይደለም፣ ፖለቲካውን የተቆጣጠሩት ስመ ጥር ፖለቲከኞች ስብስብ ነው፡፡
ስትራውስ ከ22 እስከ 30 ዓመት እድሜው ድረስ ለኒቼ ማለቅያ የሌለው አድናቆቱን፣ ሂወቱን እንዴት ተቆጣጥሮት እንደነበርና ከኒቼ አንብቦ የገባውን ሁላ ያምን እንደነበር በፃፈው ደብዳቤ ገለፆታል፡፡ (Strauss to Karl Löwith, 23 June 1935, in Strauss, Leo and Karl Löwith, “Correspondence,” Independent Journal of Philosophy, vol. 5/6, 1988, pp. 177-192.) እንግዲህ የወግ አጥባቂዎች እምነት ከኒቼ ከሆነ የፈለቀው የኒቼን ትንሽ ጥቅሶችን ለማጥናት እንገደዳለን፡፡ እንዲህ ይለናል ኒቼ፡- “አሁንስ ወዴት? አዲስ ሽብር ያስፈልገናል፡፡” (“Das Problem – wohin? Es bedarfeines neuen Terrorismus.”) (Nietzsche vol. XIV, p. 334ጉላት የተጨመረ ነው፡፡) ወይም Ecce Homoበሚለው መፅሃፉ “ለምን እጣ ፈንታ ሆንኩኝ” /“Why I am a fate”/ በሚለው ክፍል ውስጥ የሚከተለውን እናገኛለን፡- “እጣ ፈንታዬን አውቃለው፡፡ አንድ ቀን ስሜ ከአንድ የሆነ አስቃቂ ምግባር ጋር ተሳስሮ ሊወሳ ይችላል -ምድር ላይ ታይቶ ከማይታወቅ ቀውስ ጋር፣ ከጥልቅ የህሊና ግጭት ጋር፣ እስከዛ ግዜ ድረስ ሲታመን፣ ሲስፋፋ፣ ቅዱስ ተብሎ ከተያዘ ነገር ሁሉ ጋር ከሚጋጭ ውሳኔ ጋር ስሜ ሊጠራ ይችላል፡፡ እኔ ሰው አይደለሁም፣እኔ ድማሚት/በጥባጭ ነኝ፡፡”(Nietzsche vol. VII p. 317 ጉላት በፀሃፊዎቹ፡፡)
ኒቼ መካከለኛ መደቡን፣ የቤተሰብ ሂወትን፣ ኢኮኖሚያዊ ደህንነት ለማረጋገጥ የሚደረግ ጉዞን፣ እጅግ አምርሮ ነበር የሚጠላው፤ እነዚህን ሁሌም “ዝቅተኛ ሰዎች”/“last men”ከሚላቸው ጋር አያይዞ ነበር የሚያያቸው፡፡ ኒቼ ቀንደኛ የጦርነት፣ ግጭት፣ አመፃ፣ ጭካኔ አሞጋሽ ነበር፤ እነዚህን ማስቀረት እንደማይቻሉ ክስተቶች ሳይሆን አወንታዊ ዋጋ እንዳላቸው አድርጎ ነበር የሚያያቸው፡- “ብርቱነት፣ አስገዳጅነት፣ ባርነት፣ የአሳቻ ጎዳናና የልብ ውስጥ አደጋ፣ ህቡእ ሂወት፣ የሁሉን ቻይነት (stoicism)፣ ሁሉን ሞካሪነትንና የማሳሳት ጥበብ፣ ሰው ውስጥ ያለው ክፉው፣ መጥፎውና አምባገነናዊው የሆነውን ሁሉ፤ በሰው ውስጥ ያለው ከአዳኝ አውሬዎችና መርዛም እባቦች ጋር አንድ የሚያረገው ሁላ ተቃራኒያቸው ለሰው ዘር መሻሻል አስተዋፅኦ እንደሚያደርገው ይኚህም አስተዋፅኦ ያደርጋሉ፡፡” ይለናል ኒቼ፡፡ (Beyond Good and Evil 54-55)ከኒቼ ተነስተው ነው የዛሬዎቹ ገዢ ወግ አጥባቂዎች (ኦሊጋርኮች) ከጦርነትና ደም ጋር ፍቅር የተጠናወታቸው፡- “ሁሌም ጠላት እንደሚፈልጉ ሰዎች መሆን አለባችሁ – ጠላታችሁን፡፡ አንዳንዶቻችሁ በመጀመርያ እይታ ጥላቻ ይይዛችኋል፡፡ ጠላታችሁን ፈልጋችሁ ጦርነታችሁን ክፈቱበት – የአመለካከታችሁ ጦርነት፡፡ …ሰላምን መውደድ ያለባችሁ ለአዲስ ጦርነት እንደሚያገለግል አድርጋችሁ ነው፡፡ ከረዥሙ ይልቅ ደሞ አጭሩን ሰላም ውደዱ፡፡ እንድትዋጉ እንጂ እንድትሰሩ አልመክራችሁም፡፡ ድል እንድታደርጉ እንጂ ሰላም እንድታደርጉ አልመክራችሁም፡፡ ስራችሁ ውጊያ ይሁን፣ ሰላማችሁ ድል አድራጊነት ይሁን! ጦርነትን የሚያመጣው በጎ ዓላማ መነሻ በማድረግ ነው ትላላችሁ? አኔ ግን እምላችሁ፡ መልካሙ ጦርነት ነው የሁሉም ነገር መነሻ፡፡ ከርህራሄ ይልቅ ጦርነትና ወኔ የበለጠ ታላላቅ ነገሮችን አስገኝተዋል፡፡ …አስቀያሚ ናችሁ? መልካም እንጋዳውስ፣ ወንድሞቼ! ከውስጣችሁ ያለ የአስቀያሚው ካባ የሆነውን ሚስጥራዊውን / ረቂቁን ተፈጥሯችሁን ውሰዱ!”  (Zarathustra 74)
ወግ አጥባቂዎቹ በጆርጅ ቡሽ አስተዳደር እንደታዩት እራሳቸውን አክራሪ ክርስትያንና የእስራኤል ደጋፊ /ፅዮናውያን/ ክርስትያን አድርገው ያቀርባሉ፡፡ ለጦርነት እንጅ ሌላ ፋይዳ የላቸውም፡፡ ኒቼ ስለ ክርስቶስ እና ክርስትያኖች ምን ይላል፡ ክርስቶስን “ደደብ” ብሎ ይጠራዋል፡፡ (Twilight of the Idols/The Antichrist 202) ከሚታወቅበት እግዚአብሄር ሙቷል ከሚለው መፈክሩ በተጨማሪም እራሱን ፀረ-ክርስቶስ ብሎ ፈርጇል፡፡ (Ecce Homo III 2) ኒቼ ልክ እንደተከተዩ ስትራውስ የአውሮፓ ኢ-አማንያን ኒሂሊዝም ደጋፊ ነበር፡፡ ይህ አሁንም አሜሪካን የሚገዟት ወግ አጥባቂዎች የሚስጥር እምነታቸው ነው፡፡ ኒቼ ኒሂሊዝም ምን ማለት ነው ብሎ እራሱን ይጠይቅና ሲመልስ፡- “ከፍተኛ የሆኑት እሴቶች ዋጋቸው ጠፍቷል፡፡ ግቡ ጠፍቷል፡ “ለምን?” ለሚለው ጥያቄ መልሱ ጠፍቷል፡፡”(Lukacs, Von Nietzsche zu Hitler [Frankfurt am Main: Fischer, 1966], 69) እግዚአብሄር ከሞተ ሁሉ አይነት ወንጀሎች ተፈቅደዋል፡፡ ለዚህም ነው ሮበርት ካፕላን (Robert Kaplan)የእስራኤል መከላከያ ሃይል አባል የነበረ Warrior Politics በሚለው ስራው ውስጥ የአረመኔዎች የጦርነትና የጭካኔ እምነቶች ይህ ቀውስ የገነነበት አለምን ለመጋፈጥ አስፈላጊ ናቸው ብሎ ሊፅፍ የቻለው፡፡ እንደ ካፕላን አባባል በአሜሪካ አመራር ውስጥ ትክክለኛውን አመለካከት ለመቅረፅ የክርስቲያን ፍልስፍናዊና ማህበራዊ ይዘት እንቅፋት ነው የሆነው፡፡ በተጨማሪም ካፕላን የሮማው ንጉስ ቲብሪየስ (የክርስቶስ ስቅላት በዘመኑ የተፈፀመው) ታሪኩ በትክክል እንዳልቀረበ ይናገራል፡፡
ስትራውስ የኒቼን ዘር አጥፊ አመለካከቱን እያወቀ አድናቆቱን ይለግሰዋል፤ ስትራውስ What is Political Philosophy (1959)ላይ ሲፅፍ፡ “የዘመናዊው የምእራቡ ሰው ልፍስፍስ መሆንን በመረዳት [ኒቼ] ብዛት ያላቸው ሰዎችን “ምህረት የለሽ የማስወገድ እርምጃ” መብት ቅዱስነትን ሰብኳል፡፡ … ድንቅ የሆነው የመናገር ብቃቱን ተጠቅሞ አንባቢዎቹ ሕብረተሰባዊነትንና ጋርዮሻዊነትን ብቻ ሳይሆን ወግ አጥባቂነትን፣ ብሄራዊነትንና ዲሞክራሲን እንዲፀየፉ አድርጓል፡፡ ይህ ታላቅ ፖለቲካዊ ሃላፊነትን ለመሸከም ከወሰነ በኋላ፣ አንባቢዎቹን ወደ ፖለቲካዊ ሃላፊነት ተሸካሚነት የሚመጡበትን መንገድ አላመላከተም፡፡ … ለፖለቲካ ግድ የለሽ ዴንታቢስነት ወይም ሃላፊነት የማይሰማው ፖለቲካዊ ምርጫን እንዲከተሉ ነው የተዋቸው፡፡ በዚህም [እርባና ቢስነቱ] የተጋለጠው ዲሞክራሲን ዳግም እንደ ወርቃማው ዘመን እንዲታይ የሚያደርግ አገዛዝ እንዲመጣ አድርጓል፡፡ የሁለቱም የዘመናዊው ሁናቴ እና የሰው ሂወትን በፈቃደ ሃይል/will to power/ ዶክትሪኑ ለማብራራት ሞክሯል፡፡” ይለናል፡፡ በሌላ አነጋገር ስትራውስ ኒቼ የሂትለር ፈር ቀዳጅ መሆኑን ያውቀዋል፣ ሆኖም ለዛሬው ዓለም የሚሆን ፈላስፋ ነው ብሎ ይደጋፈዋል ማለት ነው፡፡
መደምደምያ
ክፍል አንድ ላይ እንዳየነው በአልበርት ፒኬ እቅድ መሰረት ሶስተኛው የአለም ጦርነት በፖለቲካዊ ፅዮናውያን እና አረቦች መካከል የሚፈጠረውን ግጭት አለማቀፋዊ በማድረግ ነው የሚጀምረው፡፡ በዚህም መሰረት ሶስተኛ የአለም ጦርነት ሽብር ላይ ጦርነት ሲታወጅ ጉዞውን አሃዱ ብሏል፤ ያነጣጠረው ግን ሽብር ላይ ሳይሆን ነፃነትንና በአንድ ፈጣሪ የሚያምኑ ሃይማኖቶችን ማጥፋት ላይ ነው፡፡ ለዚህም ነው ሽብር ላይ ጦርነት ያወጁት፡- ሽብር የችግር ምልክት ነው እንጂ ችግር አይደለምና ሽብር ላይ ጦርነት በማወጅ ማለቅያ የሌለው ዘመቻቸውን ማካሄድ ይችላሉ፡፡ ሁሉን ያካተተ ክፍት ጦርነት ካልታወጀ በስተቀር ማብቂያ የሌለው የተራዘመ ጦርነት ስለፈለጉና ችግሩ ደሞ እራሳቸው ዋይት ሃውስ የተቀመጡት ሰዎች ስለሆኑ ችግሩን ትተው ምልክቱ ላይ ጦርነት አወጁ፡፡ ማብቂያ የሌለው ጦርነት ውስጥ ህብረተሰቡ በሚከተት ግዜ ለደህንነቱ ሲል ነፃነቱን አሳልፎ ይሰጣልና፤ እንዲ ዓለም አቀፋዊ የሆነ ችግር ደግሞ ዓለም አቀፋዊ መፍትሄ ይሻል ይህም አዲስ የአለም ስርአት ያስገኛል፡፡ ይህ ንፁህ ሄግሊያዊ ዲያለክቲክ ነው፡፡ በዘመናዊ ተመራማሪዎች ችግር – አፀፋዊ ምላሽ – መፍትሄ ሂደት ይሉታል፡፡
በሄግሊያዊ ዲያለክቲክ መሰረት ማህበረሰባዊ የለውጥ ሂደት የሚገኘው ሁለት ተቃራኒ ጉልበቶች ከሚያደርጉት ግጭት በሚመጣው ውጤት ነው፣ በዚህም መሰረት ሁለት ተቃራኒ ጉልበቶችን በመፍጠርና በመቆጣጠር የውጤቱ የበላይ መሆን ይቻላል፡፡ በዚህም መሰረት ኢሉሚናቲዎች ፖለቲካዊ ፅዮናውያንንና አሸባሪዎችን በመደጎም አለምን ሁካታ ውስጥ ከተዋት ይገኛሉ፡፡ የዚህም ውጤቱ የግጭቱን ምክንያት ሃይማኖትና ዳር ድንበር (ሃገራዊ ብሄራዊነት) ላይ በማሳበብ የሚወገዱበትን መንገድ ማመቻቸት ነው፡፡
ከ9/11 በኋላ የወጣው የፀረ ሽብር ህግ ማለትም የአርበኛ አዋጅ (Patriot Act) ከጥቃቱ ቀድሞ የተሰናዳና የአሜሪካን ህገ መንግስት ለማቃወስ (ልክ ሂትለር በጀርመን እንዳደረገው) ሽብሩን ስፖንሰር ያደረጉት አካሎች ስራ ነው፡፡ አሜሪካውያን ሽብሩ የነፃነት ጠላቶች ምግባር ነው ተብለው ነው በቀጣዩ ወር 25 ጥቅምት 2001 ላይ የአርበኛ አዋጅ በም/ቤቱ እንዲፀድቅ የተደረገው፤ በዚህ አተረጓጎም አሸባሪው እግዲያ የቡሽ አስተዳደር ነው ይለናል ፖል ዋትሰን፡፡ ምክንያቱም የቡሽ አስተዳደር ያፀደቀው ህግ ለመሰረታዊ የነፃነት መርሆች የሚፃረር ነውና፡፡ (Paul J. Watson: Order Out of Chaos) ይህ አዋጅ የአሜሪካ መስራች አባቶች (Founding Fathers) የፃፉትን ህገ መንግስት የመሸርሸር ታሪክ አንዱ ክፍል ነው፡፡ አዋጁ የጣሳቸውን የአሜሪካ ህጎች መዘርዘር አያስፈልግም ባጠቃላይ ግን አሜሪካን ከነፃ ሃገር ወደ ፖሊሳዊ አገዛዝ ሃገር ነው ያሸጋገራት፡፡ በመጋቢት 13፣ 2002 ፕሬዚደንት ቡሽ ለምን አዲስ የተሾመው የደህንነት ሃላፊ የኮንግረስ አጣሪ ኮሚሽን ለጥያቄ ሲጠራው ለመቅረብ ፍቃደኛ እንዳልሆነ ሲጠየቅ መብቱ እንደሆነ ገልፅዋል፤ ይህ ሪፐብሊኳ የተመሰረተችበትን የፖለቲካ ሚዛን ያዛባ መልስ ነው፡-ህግ አውጪ፣ አስፈፃሚ፣ እና ተርጓሚ አካላትን ሚና የጣሰ ነው፣ አስፈፃሚው የፈለገውን የማድረግ መብት አለው፣ የአሜሪካ መሪ ፕሬዚደንት መሆኑ ቀርቶ ንጉሰ ነገስት ሁኗል! አሜሪካ ሉላውያን ቁንጮዎች መመስረት ለሚፈልጉት አዲስ የዓለም ስርአት እንቅፋት ነው የሆነችባቸው፡፡ ችላ ስለሚባል ልብ ልንለው ይገባልና በሪፐብሊክ እና በዲሞክራሲ መሃከል ያለውን ልዩነት እናስፍር፡-ዲሞክራሲ ማለት የብዙሃን አገዛዝ ማለት ነው፡፡ ከአምባገነን-እሚለየው የአንድ ሳይሆን የብዙሃን-ገነንነት መሆኑ ነው፡፡ ብዙሃኑ ለጥቅማቸው ሲሉ አናሳዎቹን ይረግጣሉ፡፡ የብዙሀን ስርአት-አልበኝነት ነው፡፡ ሪፐብሊክ ግን አብዝሃውም አናሳውም እኩል መብት ያለበት ገደብ የሰፈረበት የብዙሃን-አገዛዝ ሲሆን ህገ መንግስቱም መንግስት ማድረግ የማይችላቸው ወይም አብዝሃው የሚመሰርተው መንግስት የሚጣልበት ገደቦች ዝርዝር ነው፡፡ አሜሪካ ስትመሰረት በሪፐብሊክ መርሆች ነበር፡፡ ሀያሉ የብዙሀን መንግስት በሕገ መንግስት ይገራል፡፡ ዲሞክራሲ እሚለው ቃል የአሜሪካ መስራቾች በፃፉት ህገ መንግስት ላይም ሆነ አስቀድመው በፃፉት የነፃነት እወጃ ላይ አንዴም አይጠቀስም፡፡ ዲሞክራሲ የጋርዮሻውያን ሲሆን ሪፐብሊክ ደሞ የግለሰቦችን ተፈጥሯዊ፣ የማይነኩ/የማይገረሰሱ መብቶችን የሚያከብሩት ነው፡፡ ዲሞክራሲ ላብዝሃው ጥቅም ሲል አናሳዉን ይሰዋል ሪፐብሊክ ግን የአናሳዎች መብት ከመጣስ ይጠብቃል፡፡ ባጭሩ ሪፐብሊክ ብዙሃኑ የሚመሰርቱት መንግስት ላይ እሚጣል ገደብ ሲሆን ዲሞክራሲ ግን የመንጋው አምባገነንነት ነው፡፡ በአሁኑ ግዜ ዲሞክራሲ ከሸፈ እየተባለ ሰዎች ፍትህ ለማንገስ ያደረጓቸውን ሙከራዎች ለማጣጣል እየተሞከረ ነው፡፡ ዲሞክራሲ ሲጀመርም ማንም ያልፈለገው ወይም በጋርዮሻውያን ማታለያ የመጣ ሲሆን ሪፐብሊክ ግን በሰርጎ ገቦች እንዲጠፋ እየተደረገ ያለ ነው፡፡ እኚህ ሁለት ቃላቶች እንዳሻን እያቀያየርን የምንጠቀምባቸው አይደሉም፡፡ (G. E. Griifin–The Future is Calling. ይመልከቱ፡፡)
እነዚህ ቁንጮዎች የዓለምን ህዝብ ለማታለል የትኛውንም የማታለያ ዘዴ ከመጠቀም ወደኋላ እንደማይሉ ልብ ልንለው ይገባል፡፡ ይህ ክፍል ሲጀመር የጠቀስነውን የሽብር ፍቺን ያስታውሱ፡
የሽብር የመጀመርያው ወሳኝ ገፅታው በዓብዩ የሚፈፀመው የመንግስት ሽብር ነው፡፡ ሁለተኛ እንዲህ አይነቱ ሽብር መንግስት የነደፈውን የማህበረ-ፖለቲካዊ ፕሮጀክት ለማስፈፀም አብዝሃውን በማሸበር የጥቂቶችን ጥቅም ማስጠበቂያ አካል ነው፡፡
በዚህ እይታ ስንረዳው ነው እንግዲህ የ9/11እንቆቅልሾች የሚፈትሉን፡፡ ይህ ነው እንግዲህ ማህበራዊ ምህድስና ማለት፡፡ በቀጣይ ክፍል ይህ የሽብር ምህድስናቸው የሚያነግሰው መንግስት ምን አይነት ሳይንሳዊ የመቆጣጠርያ ዘዴዎችን ተጠቅሞ ዓለምን እንደሚገዛ እንፈትሻለን፡፡
Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s