ቅንጫቢ ፪ ሙስሊም ወንድማማችነት መስፋፋት (ካልታተመ መፅሃፍ የተወሰደ በግደይ ገ/ኪዳን እና ተክሉ አስኳሉ)

Posted: March 7, 2012 in ሽብር

10
ሙስሊም ወንድማማችነት መስፋፋት
በዚህ ክፍል ከሙስሊም ወንድማማችነት መስፋፋት ጋር በተያያዘ ከምእራባውያን የሚስጥር ማህበራት ጋር ያለውን ቁርኝትና የትብብር እንቅስቃሴ እናያለን፡፡ በዚህም አንባቢው ወንድማማችነቱ በእውነት እስልምናን ይወክላልን የሚለውን እንዲፈትሽ ያግዛል፡፡ ከላይ ባየነው የምእራባውያኑ አድሃሪ አጀንዳ መሰረት ተዋጊ ፅንፈኞች፣ ሁለተኛ ትውልድ ተግባሮችን እናያለን፡፡
ሁለተኛ የዓለም ጦርነት በሚጀምርበት ወቅት በግብፅ ከፍተኛ ስም ያለው የአዛም ቤተሰብ ወንድማማችነቱን በሚቀላቀሉበት ወቅት መአርጉ ከፍ አለ፡፡ አብደልራህማን ከአዛም ቤተሰብ ዝነኛው ነበር፣ ሂወቱም በጠቅላላ ለብሪታንያ ኢምፓየር ሲያገለግል ነው ያሳለፈው፡፡ ከአንደኛ ዓለም ጦርነት በውኋላ በሊብያ የሴኑሲ ወንድማማችነትን (Senussi Brotherhood) ፖለቲካዊ ስራ ከብሪታንያ ስለላ ተቋም ጋር ሲያደራጅ ነበር፡፡ (Hostage To Khomeini, Robert Dreyfuss, 1980, p. 133) ስኬታማ የነበረ ስራ ሲሆን በ1951 የሴኑሲ ወንድማማችነት መሪ ተ.መ.ድ. ባዘጋጀው የአከባበር ስነ-ስርአት የሊብያ ንጉስ ተብሎ ነግሶ ነበር፡፡ የብሪታንያ ኢምፓየር ተወዳጅ ሰው የነበረው ንጉስ ኢድሪስ ቀዳማዊ በ1969 በሞአማር ጋዳፊ እስኪገለበጥ ድረስ ሊብያን ገዝቷል፡፡ የጋዳፊ አብዮታዊ ሃይሎች እራሳቸው በ1966 ለንደን ውስጥ ነበር የተደራጁት፣ ምንም እንኳ የጋዳፊ አስተዳደርም ወዲያው ከብሪታንያ የሚሰጠው ፍቅር ቢቀዘቅዝበትም፡፡
ከሁለተኛ ዓ.ጦ. በኋላ አብደልራህማን አዛም ብሪታንያ ስፖንሰር ያደረገችው የዓረብ ሊግ (League of Arab States) ዋና ፀሃፊ ሁኖ ተሾመ፡፡ የአዛም የክብር መአርግ ከፍተኛነት የሚመዘነው ሙና የተባለች ልጁ የሳውዲ ዓረቢያውን ንጉስ ፈይዛል የመጀመርያውን ልጅ መሀመድ እንድታገባ ከመደረጉ ነው፡፡ (Biography of Ayman al-Zawahri)
በ1955 ጀነራል ናስር ሙስሊም ወንድማማችነትን በሚያፈርስበት ወቅት ድርጅቱ ዋና እንቅስቃሴ ማእከሉን ወደ ለንደንና ጀኔቫ አዛወረ፡፡ የጀኔቫው ቅርንጫፍ ሰዒድ ረመዳን፣ ይህ ሰው የሀሰን አልበናን ልጅ ያገባ ሲሆን የእስላማዊ ጥናቶች ተቋምንም የመሰረተ ነው፡፡ በርሱ እይታ ስርም ጀኔቫ ዋና የአውሮፓ እስላማዊ ማእከል ለመሆን ችላለች፡፡ ከስር የተጠቀሰው አንቀፅ ረመዳን ከህቡእ እስላማዊ እንቅስቃሴዎች ጋር ያለውን ትስስር ያስረዳናል፡-
ከኢራን አብዮት ማግስት የአያቶላ መንግስት ተቃዋሚዎች ዋነኛ ድምፅ ሆነ፡፡ በሻሃ ስር በዋሽንግተን ዲ.ሲ. ኢራን ኢምባሲ የመረጃ መማክርት ነበር፡፡ ከሻሃው መውረድ በኋላ የኢራን ነፃነት ፋውንዴሽንን መስርቷል፡፡ በሐምሌ 1980በዴቪድ ቤልፊልድ ወይም ደግሞ በሌላ ስሙ ዳዉድ ሳላዲን ተገደለ፡፡ ቤልፊልድ ጥቁር ሙስሊም ሲሆን ከአያቶላ የዋሽንግተን የሚስጥር ደህንነቶች (Savama)ሃላፊ ነው የሚባለው ባህራም ናሂድያን ጋር ከሚገናኙ ቡድኖች ጋር ግንኙነት ነበረው፡፡ ከግድያው በውኋላ ሁለት ሰዓታት ባልበለጠ ግዜ ውስጥ ቤልፊልድ በቀጥታ ለሰዒድ ረመዳን ጀኔቫ ስልክ ደውሎለታል፤ ቀጥሎም የተለያዩ ፓስፖርቶችን በመጠቀም ዩናይትድ ስቴትስን ለቆ ሰስዊዘርላንድ ሂዷል፡፡  (Hostage To Khomeini, Robert Dreyfuss, 1980, pp. 174-175)
ጀኔቫ ለሙስሊም ወንድማማችነት ጠቃሚ ቦታ ብትሆንም ለንደን ግን ዋናዋ ነች፡፡ እዚህ ዋናው ሃላፊ አብደልራህማን አዛም ነው፡፡ ከላይ እንደተጠቀሰው ከሰዒድ ረመዳን ጋር በመተባበር ለንደን ውስጥ በ1973 የተመሰረተው የአውሮፓ እስላማዊ መማክርት ሃላፊ ነበር፡፡ ድሬፈዝ የመማክርቱን ሚና እንዲህ ያብራራዋል፡-
“…[መማክርቱ] ከሞሮኮ እስከ ፓኪስታን እና ህንድ ድረስ ኢክዋንን [ወንድማማችነቱን] ይመራዋል፤ በምእራብ አውሮፓ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሃይማኖታዊ ማእከሎችን በመቆጣጠር፣ በነርሱ ደግሞ በመካከለኛው ምስራቅና በአውሮፓ የሚገኙ በሺዎች የሚቆጠሩ ፅንፈኛ ተማሪዎችና የሃይማኖት መሪዎችን ይቆጣጠራል፡፡”(Hostage To Khomeini, Robert Dreyfuss, 1980, p. 160)
በ1978 የመከላከያ ቴክኖሎጂ እስላማዊ ተቋም –Islamic Institute for Defense Technology—IIDT“የቀውስ መክብብ” አብዮቱን ሊረዳ ተመሰረተ፡፡ ከኔቶ NATO- ጋር በጥምረት እንዲሰራ በሳሌም አዛም እና የአውሮፓ እስላማዊ መማክርት ነበር የተመሰረተው፡፡ ፓኪስታንና አፍጋኒስታን ቁጥር አንድ አጀንዳው የነበሩ ሲሆን በመካከለኛው ምስራቅ ዙርያ ሙስሊም ወንድማማችነት ሲያደርግ የነበረውን ትግል ለመርዳት ብዛት ያለው መሳርያ በማቀበል ሲያስተባብር ነበር፡፡(Hostage To Khomeini, Robert Dreyfuss, 1980, p. 164)
ከግብፅ ውጪ ለዘብተኛ አቋም ያላቸውና አመፃን ያወገዙ የተለያዩ ግንባሮችን በማቋቋም መልካም ስም በማፍራት ተሳክቶለታል፡፡ በግብፅ ውስጥ ግን የሙስሊም ወንድማማችነት መንግስትን ገልብጦ “ንፁህ” እስላማዊ መንግስት የመመስረት እቅድ ሲያንፀባርቅ ይህን ዒላማ ለማሳካትም ሽብርን በዋናነት ይጠቀማል፡፡ አንዋር ሳዳት የግብፅ ፕዚደንት ሲሆን ወደ ሙስሊም ወንድማማችነት ያለውን አቋም ማለሳለስ ጀመረ፡፡ የሙስሊም ወንድማማችነት የበላይ መሪ (Supreme Guide) ሁሌም ተቀማጭነቱን በግብፅ የሚያደርግ ሲሆን፣ አብዛኞቹ አመራሮች እና አባሎች ግን በውጪ ናቸው የሚቀመጡት፡፡ የበላይ መሪው ተምሳሌታዊ እንጂ ዋናው የህቡእ እንቅስቃሴው መሪዎች ተቀማጭነታቸው ለንደንና ጀኔቫ ናቸው፡፡
ታፍኪር ዋል ኸጂራ በህቡእ ካሰማራቸው ቡድኖች አንደኛው ነው፡፡ ሹሪክ አህመድ ሙስጠፋ የተባለ የሙስሊም ወንድማማችነት አባል የነበረ ሚመራው ሲሆን በ70ዎቹ ነው የተመሰረተው፡፡ በ1977 የሃይማኖት ሚኒስትር የነበረን በመጥለፍ እንዲለቀቅ ከተፈለገ ስድስት እስረኞች እንዲለቀቁላቸውና 200,000 የግብፅ ፓውንድ እንዲሰጣቸው ጠየቁ፡፡ ጥያቄያቸው ሳይመለስ ሲቀር የሼኩን አስከሬን ሰጡና ተከታታይ የቦምብ ጥቃቶች ፈፀሙ፡፡ አባሎቹ ከነመሪያቸው የታሰሩ ሲሆን ያሸባሪዎቹ ቡድን ህልውና ግኝ ቀጥሏል፡፡ (Holy War, Wilhelm Dietl, 1983, pp. 64-66) የእስላማዊ ነፃነት ድርጅትየተሰኘ ደግሞ ሌላኛው በቀድሞ የሙስሊም ወንድማማችነት አባል ዶ/ር ሳሌህ ሲሪያ የተመሰረተ ቡድን ነው፡፡ የቡድኑ አባሎች በ1974 የወታደራዊ አካዳሚን በመቆጣጠር፣ መሳርያዎችን በመያዥ ሳዳት ሲናገርበት ወደነበረ ህዝባዊ መድረክ በማምራት ጥቃት ለመፈፀም ሞክረው ነበር፡፡ እቅዳቸው ከሽፎ ሲሪያ ተይዞ በሞት ተቀጣ፡፡ (Holy War, Wilhelm Dietl, 1983, p.66) ሁለት ዋነኛ ከሙስሊም ወንድማማችነት የመነጩና እስከአሁን ድረስ የሚንቀሳቀሱ የሽብር ቡድኖች ጀማት አልኢስዝላሚያ ማለትም እስላማዊ ቡድን እና የግብፅ እስላማዊ ጂሃድ ወይም ባጭሩ ጂሀድ ወይም አልጂሀድ የሚባሉት ናቸው፡፡ ሁለቱም ቡድኖች በአንዋር ሳዳት ግድያ እጅ አላቸው፡፡ ጀማት አልኢዝላሚያ ከሊብያው መሪ ጋዳፊ ጋር ባሳየው መተባበር ሳዳትን ለማወክ በ1971 ነው የተቋቋመው፡፡ የሙስሊም ወንድማማችነት አባል በሆነ ሂለሚ አልጋዛር የሚመራ ሲሆን ሲጀመር ከአመፅ እራሱን በማራቅ በዩኒቨርሲቲ አካባቢዎች ይንቀሳቀስ ነበር፡፡ ይህ ግን ወድያው ተቀይሯል፡፡ አይነስውር የሆነ ሼክ ዶ/ር ኦማር አህመድ መሀመድ አብደልራህማን የተባለ በኋላ መሪ ሁኖ ብቅ አለ፡፡ (Holy War, Wilhelm Dietl, 1983, p.67) ሌላኛው ኢዝላሚክ ጂሃድ የተባለው መጀመርያ በ1977 አልአህራም ጋዜጣ ሰማንያ አባሎቹ መታሰራቸውን ሲዘግብ ነበር ወደ ህዝብ አይን የመጣው፡፡ በወቅቱ ከአባላቱ አንዱ የነበረው አይማን አልዛዋሂሪ ነው፣ ወጣት የላይኛው መደብ ቤተሰብ አባል የሆነና የአዛም ቤተሰቦች ዘመድ የሆነው፡፡ (ዛሬ ይህ የአልቃይዳ ቁጥር አንድ የሆነ ሰው ነው፡፡) ሴት አያቱ ስንጀምር ያነሳነው ታዋቂው አብደልራህማን አዛም እህት ነች፡፡ አጎቱ ደግሞ የአውሮፓ እስላማዊ መማክርቱ ሳሌም አዛም ነው፡፡ የግብፅ አቃቤ ህግ ቡድኑን “ፅንፈኛ የአሸባሪዎች ቡድን” በማለት ሲገልፀው “ከውጭ የሚደጎም ሲሆን፣ ትጥቅ፣ ፈንጂ፣ እና ቴክኒካዊ መሳርያዎችንም ያገኛል፡፡” ብሏል፡፡ (Holy War, Wilhelm Dietl, 1983, p. 68, also see Zawahiri biography)
ሳዳት ከመገደሉ ከሁለት ዓመት በፊት የሙስሊም ወንድማማችነት ዓለምአቀፍ ኮሚቴ ለንደን ውስጥ ስብሰባ ያደረገበት ግዜ ነበር፡፡ የወንድማማችነቱ መሪዎች ከግብፅ፣ ሱዳን፣ ጆርዳን፣ ፓኪስታንና አፍጋኒስታን የተሰባሰቡ ሲሆን፣ በወቅቱ በፓኪስታንና ኢራን ያገኙትን ስኬትና የአፍጋኒስታን፣ ሶርያንና ግብፅን እጣ ፈንታ ሲወያዩ ነበር፡፡ (Holy War, Wilhelm Dietl, 1983, p. 61) በግብፅ ሳዳት የአቋም መለሳለሱን ሲገፋበት ነበር፡፡ በ1978 የሙስሊም ወንድማማችነት ህትመት የሆነውን አልዳዋ እንዲሰራጭ ፈቀደ፡፡ በ1979 ከበላይ መሪው ኦማር ኢልተልሚሳኒ ጋር ተገናኝቶ ቢወያይም ሙስሊም ወንድማማችነት ሳዳት ላይ በህትመትና በመስጊዶች የሚያወርደውን ወቀሳ አልቀነሰም፡፡ በስተመጨረሻ ሳዳት ከመገደሉ ከሳምንታት በፊት ኢልተልሚሳኒ አሳስሮት የነበረ ሲሆን አልዳዋም እገዳ ወርዶበት ነበር፡፡
ሳዳት የተገደለ ግዜ በግብፅ የሙስሊም ወንድማማችነት ቀንደኛው ተጠሪ ከማል አልሳናኒሪ ነበር፡፡ መንግስት ይዞ በሚመረምርበት ግዜ የሞተ ሲሆን መንግስት እራሱን አጠፋ ሲል ባለቤቱ ግን አልተቀበለችውም፡፡ ባለቤቱ የሰይድ ኩትብ (ከአልበና ቀጥሎ ቀንደኛው የሙስሊም ወንድማማችነት ንድፈ-ሃሳባዊው) ልጅ ነች፡፡ ሌላው ተጠርጥሮ የታሰረው አይነ ስውሩ ሼክ ኦማር አብዱልራህማ ሲሆን በነፃ ተለቋል፡፡ መንግስት በኢ-አማንያንና መናፍቃን ነው የሚመራው በማለት ገዳዮቹን የሚያበረታታ ንግግር አድርጓል፡፡ ዓላማቸውን ለማሳካትም መስረቅ እንደሚፈቀድላቸውና መንግስትን መገልበጡ ከተሳካላቸው ደግሞ በባለስልጣናቱ ሚስቶች ላይ የፈቀዱትና ማድረግ እንደሚችሉም ተናግሯል፡፡ (Holy War, Wilhelm Dietl, 1983, p. 87) ከዘመናት በውኋላ ደግሞ በ1993 የኒው ዮርኩ የዓለም ንግድ ማእከልን (World Trade Center) (“አልቃይዳ በመስከረም 11 ጥቃት ያፈረሰውን” በትእምርተ ጥቅስ ምልክት ያስገባንበት ምክንያት በኋላ ይገለፃል፡፡) ቦምብ ጥቃት በመፈፀም ተከሶ ነበር፡፡ ሁለት ልጆቹ አልቀይዳን በመቀላቀል ዋና የቢንላደን ተከታዮች ሁነዋል፡፡
አይማን አልዛዋሂሪም ከሶስት አመት እስር በኋላ በመለቀቅ የኢዝላሚክ ጂሀድ መሪ ሁኗል፣ በኋላም ከኦሳማ ቢን ላደን አልቃይዳ ጋር ተጣምሯል፡፡ ግብፅን ከለቀቀ በኋላ መቀመጫውን ጀኔቫ፣ ስዊዘርላንድ ነበር ያደረገው፣ ሙስሊም ወንድማማችነት በሚቆጣጠረውና ሰዒድ ረመዳን በሚመራው እስላማዊ ማእከል ጥላ ስር በመከለል፡፡ (Bin Laden: The Man Who Declared War On America, Yossef Bodansky, 1999, p. 101, p. 125) አሁን ዛሬ አልዛዋሂሪ የአልቃይዳ ቁጥር አንድ ሰው ሁኖ ወጥቷል፡፡ ከወንድሙ መሀመድ አልዘዋሂሪ ጋር በመሆን ከሙስሊም ወንድማማችነት ጋር የጠበቀ ግንኙነት ያላቸው ሲሆን በአንድ ወቅት ሙስሊም ወንድማማችነት በግብፅ ለሚካሄደው አብዮት በቂ ድጋፍ አያደርግም ብሎ በመተቸቱ ወንድማማችነቱ እራሱን በለዘብተኝነት ጭንብል ለመሸፈን እንደ ማስረጃ ይጠቀምበታል፡፡ ሌላኛው በአልቃይዳ ቁልፍ ቦታ ያለውና ከሳዳት ግድያ ጋር ግንኙነት ያለው የገዳዩ ካሊድ ኢዝላምቡሊ ወንድም ነው፡፡ አህመድ ሻውቂ አልኢዝላምቡሊ ግብፅን ለቆ ካራቺ፣ ፓኪስታን ተከሰተ፡፡ እዚህም የህቡእ አዘዋዋሪዎችን መርበብ ማቋቋም ላይ ሲረዳ ነበር፡፡ በኋላ በሱዳን ከቢን ላደን ጋር ሶማልያ ላይ የፅንፈኞች የጦር ሰፈር መመስረት ላይ ሲሰራ ነበር፡፡ በኋላም የቢንላደን ፀረ-አይሁድና መስቀለኛ ጦረኞች የዓለም እስላማዊ ግንባር ለጂሃድ የተባለ ቡድን ውስጥ አባል ሆነ፡፡ (Bin Laden: The Man Who Declared War On America, Yossef Bodansky, 1999, p. 13, p. 405) (ይህ ፅሁፍ በሚዘጋጅበት ግዜ በሶማልያ የሚንቀሳቀሰው ፅንፈኛ ቡድን አልሸባብ ከአልቃይዳ ጋር መቀላቀሉን የፋ ያደረገ ሲሆን አላዛዋሂሪም የቅበላ ንግግሩን አሰምቷል፡፡ ይህ ሽብርን የቀጠና ጦርነት ለመዝራት ጥቅም ላይ ሲውል የሚያሳይ ሲሆን የም/አፍሪካ ሃገራት በሶማልያ ጉዳይ እጃቸውን ማስገባታቸው ጥቃቱን በሃገራቱ እንዲያሰፋ ሰበብ ይፈጥርለታል፡፡ ቼክ ሜት!)
በቅርብ የመጣው ከሙስሊም ወንድማማችነት የመነጨው ፅንፈኛ ቡድን ፍልስጤም የሚገኘው ሃማስ ነው፡፡ በ1988 ሼክ አህመድ ያሲን “እስላማዊ ቃልኪዳን”/“Islamic Covenant” ከፃፈ በኋላ ነው ይፋ የሆነው፡፡ ለብዙ አመታት በጋዛ የሙስሊም ወንድማማችነት ሃላፊ ነበር፣ ቡድኑ ከ1978 ጀምሮ ይንቀሳቀስ የነበረ ሲሆን ስማቸው ሙጀማ አልኢስላሚ ይባላል፡፡ ቡድኑ በ1988 ባሳተመው “እስላማዊ ቃልኪዳን” መሰረት እራሱን “የሙስሊም ወንድማማችነት የፍልስጤም ቅርንጫፍ”በማለት ይገልፃል፡፡(Hamas background, profile) ሮበርት ድረይፈዝ ስለሙስሊም ወንድማማችነት ድርጅት ባህርያት ከስር ባጭሩ ያስቀምጥልናል፡፡ በ1980 የተፃፈ ሲሆን ዛሬም ከሰላሳ አመት በኋላ እውነት ናቸው፡
እውነተኞቹ ሙስሊም ወንድማማችነት አክራሪው ሼክ ወይም ከሱ እኩል አክራሪ የሆኑ ተከታዮቹ አይደሉም፣ ወይም የነዚህ እብድ ሰዎችን አጠቃላይ እንቅስቃሴ የሚመሩት ከላይ ያሉት ሙላዎች እና አያቶላዎችም አይደሉም፤ ኮሚኒ፣ ጋዳፊ፣ ጀነራል ዚያ በሚያምር መልኩ የተቀረፁ አሻንጉሊቶች ናቸው፡፡
እውነተኞቹ ሙስሊም ወንድማማችነት እጃቸውን በመግደልና በማቃጠል አያቆሽሹም፡፡ ከመጋረጃው በስተጀርባ የሚቆሙት ባንከኞችና ደጓሚዎች ናቸው፣ የዘር ሃረጋቸው የጥንት የዓረብ፣ የቱርክ ወይም የፐርሺያ ቤተሰቦች ገዢ መደብ ቁንጮዎች(oligarchical elite) የሆኑት፣ ከአውሮፓው ጥቁር መሳፍንት (black nobility) ጋር በተለይ ከብሪታንያ ገዢ ቡድኖች (oligarchy) ጋር ምቹ የቢስነስና መረጃ/ስለላ ትስስር ያላቸው ናቸው፡፡
በተጨማሪም ሙስሊም ወንድማማችነት ገንዘብ ነው፡፡ በአጠቃላይ በተንቀሳቃሽ ጥሬ ገንዘብ/ንዋይ ወንድማማችነቱ በአስርት ቢሊዮኖች የሚቆጠር ዶላሮችን ይቆጣጠራል፣ በተጨማሪም በእለተለት የቢዝነስ እንቅስቃሴ ከነዳጅ ንግድና ባንክ ስራ እስከ እፅ ማዘዋወር፣ ህገወጥ የትጥቅ ማዛወር፣ የወርቅና አልማዝ ማዛወር ስራ በቢሊዮኖች ዶላሮችን ያንቀሳቅሳል፡፡ የአንግሎ-አሜሪካ ተቋም [የሚስጥር ማህበሩ] ከሙስሊም ወንድማማችነት ጋር በመወዳጀት ቅጥረኛ አሸባሪዎችን ሁካታ ብቻ አይደለም የሚሸምቱት፣ ሃያልና አለም ዓቀፍ በሆነ ከስዊዝ ባንክ ሂሳብ እስከ ከቁጥጥር /እይታ ነፃ የሆኑት የዱባይ፣ ኩዌትና ሆንግ ኮንግ ድረስ የሚደርስ የፋይናንስ ኢምፓየር ውስጥ አጋሮች ነው እየሆኑ ያሉት፡፡”(Hostage To Khomeini, Robert Dreyfuss, 1980, pp. 164-165)

አሁን አንባቢው ፅንፈኛ እስላማዊ እንቅስቃሴው ምነኛ ከሚስጥር ማህበራቱ ጋር የተሳሰረና ከሙስሊም ወንድማማችነት ጋር የተገናኘ መሆኑን መመልከት መጀመሩን ተስፋ እናደርጋለን፡፡ የኦሳማ ቢን ላደን ሂወት ሲጠና ይበልጥ ግልፅ ይሆናል፡፡

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s