የዋጋ ንረት ጥያቄ፡ የዕቃ አቅርቦት፣ የገበያ ሥርዓት ያለመዘመን፣ ወይስ የገንዘብ አቅርቦት?

Posted: March 6, 2012 in ፋይናንስና ኢኮኖሚ

የዋጋ ንረት ጥያቄ፡ የዕቃ አቅርቦት፣ የገበያ ሥርዓት ያለመዘመን፣ ወይስ የገንዘብ አቅርቦት?

በግደይ ገብረኪዳን

ይህችን አጭር መጣጥፍ ወይም የሙከራ ጽሑፍ እንድጽፍ ያነሳሳኝ የተሻለ ዕውቀት ስላለኝ ወይም ከሌላው በከፋ መልኩ የዋጋ ንረት ኪሴን ስለጎዳው አይደለም፡፡ እንደ ታዘብኩት ከሆነ በዋጋ ንረት ዙርያ ያለው ከፍተኛ ሙያዊ ትንተና እጥረት ባለችኝ ዕውቀት እየተወላገድኩም ቢሆን ካለው ያበረከተ ንፉግ አይባልምና የአቅሜን ልበል ከሚል ነው፡፡

ማንኛውም ሥራ ይህችን የማትረባ መጣጥፍ ጨምሮ የሚሠራው በሁለት ስሜቶች ተሞርክዞ ነው፡፡ ከጥላቻ በመነሳት ወይም ከፍቅር፡፡ ማንኛውንም ዓላማ የያዘ ሰው ከጥላቻ በመነሳሳት አጋጣሚዎችን በመጠቀም የወቀሳ ጣቶቹን ለመጠቆም ተነሳስቶ የሚሠራ ከሆነ ከጅምሩ የከሰረ መንገድ ውስጥ የገባ ነው፡፡ በአንጻሩ ከፍቅር በመነሳት እውነትን ለማወቅ እስከ ጥግ ለመጓዝ ፈቃደኛ የሆነ ግን ጉዞው አስቸጋሪ ቢሆንበትም ከፈለገው ግብ መድረሱ ሽልማቱ ነው፡፡ ስለዚህም ይህች መጣጥፍ በዚህ ስሜት እንድትነበብ እጠይቃለሁ፡፡

የዋጋ ንረት የሰው ልጆች እንዲያውቁት ከተፈቀደው በላይ ከገንዘብ አቅርቦት (Money Supply) ጋር ግንኙነት አለው፡፡ ገንዘብ ከተፈጠረ ሺሕ ዘመናትን ያስቆጠረ፣ ለመፈጠሩ መንስዔው አየር ለሳንባ የሚያስፈልገውን ያህል ለመረዳት እጅግ ቀላል የሆነ፣ ነገር ግን በምንነቱ ላይ ምሁራን የሚባሉት መግባባት ላይ ሊደርሱበት ያልቻሉት፣ በተራው ሕዝብ ዘንዳ ደግሞ ለመረዳት የአንስታይንን የሪላቲቪቲ ንድፈ ሐሳብ ያህል የሚያስፈራ ርዕሰ ጉዳይ ከሆነ ዘመናትን አሳልፏል፡፡

ካንገብጋቢው የኪስ መዳከም ጉዳይ ተፈናጠርክ አትበሉኝና የሚከተለውን ጥያቄ  አድምጡኝ፡፡ ገንዘብ ምንድን ነው?  ይህን እንቆቀልሽ መፍታት ካልቻልን ስለዋጋ ንረት የማውራት ፈቃድ ሰጪ ቢኖር ኖሮ ይሁንታውን ይነሳን ነበር፡፡ ዛሬ ገንዘብ ‹‹ላምጭው እንዲከፈል ሕግ ያስገድዳል›› የሚል የተጻፈበት በማተሚያ ቤት ያለፈ ወረቀት ከመሆን ደርሷል፡፡ ይህ እንዴት ሊሆን እንደቻለ ለመረዳት ደሞ የገንዘብ አፈጣጠርን ማወቅ ሊኖርብን ነው፡፡ አሁንም በረዥሙ ወደኋላ እንድንጓዝ የሚያስገድደን ስለሆነ በትዕግስት ይከተሉኝ፡፡

ሰዎች የፈለጉትን በሙሉ ማምረት አይችሉምና በግላቸው የሠሩትን እርስ በርስ መቀያየር ግድ ይላቸው ነበር፡፡ ከብት አርቢው ከእህል አምራቹ ጋር፣ እነዚህም ከሸማኔው ጋር፣ መልሶም ከጌጣጌጥ ሠሪው ጋር እንደየፍላጎታቸው እየተገናኙ ምርቶቻቸውን ይለዋወጡ ነበር፡፡ (እነዚህ ንብረቶች በራሳቸው እሴት ያላቸው የሚባሉ ሲሆኑ የቃሉ ትርጉምም መገበያያ ቦታ ባይወሰዱ ለባለቤቶቻቸው ጥቅም የሚሰጡ ማለት ነው፡፡ ይህም ከወረቀት ገንዘብ ጋር ሲነፃፀር ሕግ ባያስገድድ ኖሮ የወረቀት ገንዘብ በራሱ ጥቅም መስጠት አይችልምና በራሱ እሴት የሌለው እንዲባል ያደርገዋል፡፡) በራሳቸው እሴት ያላቸውን ምርቶቻቸውን ይዘው የፈለጉትን አግኝተው መቀያየራቸው ግድ ቢላቸውም፣ ንብረቶቻቸውን ይዞ መዞር ግን የራሱ ግልጽ የሆነ ደካማ ጎንም አለው፡፡ እንደልብ ለማጓጓዝ አይመችም፣ ለረዥም ጊዜ ለማቆየት አይመችም ወዘተ….፡፡

ስለዚህም ሁሉም በተደጋጋሚ የሚፈልጋቸውና በራሳቸው እሴት ያላቸው ንብረቶች ሁሉንም መለወጫ ወይም መገበያያ ማለትም ገንዘብ መሆን ጀመሩ፡፡ ለምሳሌ እንደ ጨው ያለውን እናስታውሳለን፡፡ ይህ እንግዲህ በጥንት ጊዜ ሲሆን፣ የ17ኛው ክፍለ ዘመንን ምሳሌ ብናነሳ ደግሞ ገዢዎቿ ወጪያቸውን ለመሸፈን ያለአግባብ ብዙ ገንዘብ አትመው በማሰራጨታቸው፣ ገንዘቡ የመግዛት አቅሙ ሲጠፋ የትንባሆ ቅጠል በአሜሪካ ግዛቶች ገንዘብ ለመሆን ችሎ ነበር፡፡ ከቅርብ ዘመን ደግሞ በጀርመን በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጊዜ በተመሳሳይ የገንዘባቸው የመግዛት አቅም ሲወርድ ሲጋራ መገበያያ ለመሆን በቅቶ ነበር፡፡ ምንጊዜም ዋጋቸው የማይዋዥቅና ሁሉም የሰው ዘር የሚቀበላቸው የከበሩ ማዕድናት (ወርቅ፣ ብርና ነሐስ) ግን አስተማማኝ ዋስትና ሆነው፣ በአቅርቦትና ፍላጎት ሕግ ተመርተው፣ በራሳቸው እሴት ያላቸውን ማናቸውንም ንብረቶች መቀየርያ መሣርያ ማለትም ገንዘብ ለመሆን በቅተው ነበር፡፡ አንድ ሜትር ከመቶ ዓመት በፊትና ዛሬ እኩል ነው፡፡ የሚገርመው በሮማውያን ጊዜ ሙሉ ልብስ መግዛት የሚችለው የወርቅ ሚዛን ዛሬም ሙሉ ልብስ ይገዛል፡፡ ከመቶ ዓመት በፊት ሙሉ ልብስ የሚገዛው የአቅርቦትና የፍላጎት ሕግ ወይም የገበያ ሕግ የማይከተለው የማተሚያ ቤት ውጤት የሆነው የወረቀት ገንዘብ ግን፣ ዛሬ ላይ ሙሉ ልብስ ለመግዛት እጥፍ ድርብ ጭማሪን ይጠይቃል፡፡ በሌላ አነጋገር ካልሲም አይገዛም፡፡

ታድያ ለምንድነው እንደ ሜትር አስተማማኝ የሆነው በገበያ የሚለኩት የከበሩ ማዕድናት የመገበያያ ገንዘብ የማይሆኑት? እንዴት ብለው ነው የሰው ልጆች ወደዚህ ተለጣጭ የወረቀት መለኪያ ሾልከው የገቡት?

ይህ ጥያቄ ወደ ባንኮችና ፖለቲከኞች ወደ ተሻረኩበት የገንዘብ የምሥጢር ሳይንስ ያስገባናል፡፡ የከበሩ ማዕድናት አስተማማኝ የዋጋ መለኪያ ከሆኑ በኋላ ለፍቶ ያገኛቸው ሰው የዘራፊዎች ሲሳይ እንዳይሆን፣ ከወርቅ አንጥረኞች ቤት እየከፈሉ ማስቀመጥ ጀመሩ፡፡ አንጥረኞቹ አስተማማኝ ሳጥን (ቮልት) ባለቤቶች ናቸውና፡፡ በምትኩ ወርቅ አስቀማጩ ደረሰኝ ይሰጠዋል፡፡ ደረሰኙ ላይ ይህ ደረሰኝ በእገሌ ቤት የተጠቀሰውን ያህል ወርቅ የማስቀመጡ ማስረጃ ነው ወዘተ. የሚል ጽሑፍ ይሰፍርበታል፡፡ የደረሰኙ ባለቤትም የፈለገውን ሊገዛ ሲሻ ንብረቶቹን ለሚሸጥለት ነጋዴ ወርቅ ከእገሌ ቤት ውሰድ ብሎ ደረሰኝ ቆርጦ ይሰጠዋል፡፡ ነጋዴውም ከተባለው ወርቅ ቤት በመሄድ ካሻው ወርቁን ይወስዳል፣ ወይም ወርቁን ወደ ራሱ ሳጥን አዛውሮ ሌላ የራሱን ደረሰኝ ይቀበላል፡፡ እነዚህን ደረሰኞች እንግዲህ መቶ በመቶ በወርቅ (በከበሩ ማዕድናት) ዋስትና የተገባላቸው ናቸው፡፡ ወይም ብላሽ ወረቀት ሳይሆኑ ይህን ደረሰኝ ባመጡ ጊዜ በወርቅ ይቀየርልዎታል የሚባሉ ናቸው፡፡

ይህንን የመሰለ ድንቅ ክስተት ምን አጠፋው? ወርቅ አንጥረኞቹ አንድ ነገር ልብ አሉ፡፡ ወርቃቸውን ያስቀመጡት ሰዎች ከሚያስቀምጡት ከፊሉን ብቻ ሲሆን የሚያወጡት፣ አብዛኛው እዚያው የሚቀመጥ ነው፡፡ ስለዚህ ባንከኞቹ ከወርቅ አንጥረኞች ተቀብለው ያስቀመጡት ወርቅ ዝም ብሎ ከሚቀመጥ መሥራት ለሚፈልግ አናበድረውም? በማለት ለብድር ፈላጊዎች ደረሰኝ እየጻፉ ሌላ ሰው ያስቀመጠውን ወርቅ ዋስ በማድረግ የገቢያቸውን አድማስ አሰፉ፡፡ ይህም ማለት እንደ አጋጣሚ የዚያን ቤት (ባንክ) ደረሰኝ የያዙ በሙሉ መጥተው በወርቅ ቀይሩልን ቢሉ፣ ካለው ወርቅ በላይ ደረሰኝ ስላተሙ ለሁሉም መመለስ አይችሉም፡፡ እንዲህ ዓይነት ሁኔታ የሚገጥመው ወርቅ አስቀማጮቹ ጥርጣሬ ሲገባቸውና የነበረው መተማመን ሲሸረሸር ወርቃቸውን ለማዳን እየተሽቀዳደሙ ከወርቅ ቤቱ ሄደው ወርቃቸውን ሲጠይቁ ነው፡፡ ወርቅ አንጥረኛው ያለአግባብ ብዙ ደረሰኝ ያተመ እንደሆን  ኪሳራ ውስጥ ገብቶ በኃፍረት ደጆቹን ዘግቶ ከሥራ ውጪ ይሆናል፡፡ ገሚሶቹን አስቀማጮችንም ያከስራል፡፡ ይህ እንግዲህ በከፊል ብቻ ወርቅ ዋስ የሆነውን ገንዘብ የሚመለከት ነው፡፡ ግን ታሪኩ ከዚህም ይብሳል፡፡

ባንኮቹ ሥርዓት አድርገው ገበያው ያመጣላቸውን ብቻ በመቀበል ከመኖር፣ ከፖለቲከኞች ጋር በመመሳጠር የላይኛውን ዓይነት ኃፍረት የሚያመልጡበትን መንገድ ማመቻቸት ጀመሩ፡፡ ባንከኞች ለመጀመርያ ጊዜ በእንግሊዝ አገር እ.ኤ.አ በ1694 የእንግሊዝ ባንክ (ባንክ ኦፍ ኢንግላንድ) የተሰኘ ተቋም በመመሥረት የፈለገውን እንዲያትም፣ ያተመውም ሕጋዊ መገበያያ እንዲሆንና ያለዚህ ተቋም በስተቀር ሌላ ቦታ ወርቅ ማስቀመጥ በመከልከል የመጀመርያውን የማዕከላዊ ባንክ ውልደት አስገኙ፡፡ ንጉሡና የፓርላማ አባሎች ተሽቀዳድመው ከዚህ የግል ማዕከላዊ ባንክ ድርሻ ገዙ፤ መንግሥትም ጦርነትን ለመደጎም ከዚሁ መበደር ጀመረ፡፡  የጦርነት ወጪውን ሕዝቡ በቀጥታ በግብር እንዲሸፍን ቢደረግ ውዝግብ ያስነሳልና፡፡ ይህ አዲስና ከምንም ተነስቶ ሀብት የማግኛ ሚስጥር ለባንከኞቹና ፖለቲከኞቹ ታላቅ የምሥራች ሆነላቸው፡፡

የወርቅ ዋስትናው መጠን ሲጀመር መቶ በመቶ የነበረውን (ማትም የከበሩ ማዕድናት ገንዘብ) እየሸረሸሩ (በከፊል ዋስ የሆነ ገንዘብ) በማምጣት ቀጥለው፣ ዛሬ የምናውቀው ምንም ዋስትና የሌለው ሕግ ብቻ የሚያስገድደው የደረሰኝ ገንዘብ (ፊያት መኒ) ላይ ሊያደርሱን ችለዋል፡፡

በሕግ የሚያስገድድ ገንዘብ መንግሥት ከሕዝብ ጋር ሳይጨቃጨቅ ወጪዎቹን ለመሸፈን በማተም የሚጠቀምበት አቋራጭ መንገዱ ነው፡፡ ወርቅ ዋስትና ይሁነው ቢባል ኖሮ ጥሩ ልጓም ይሆን ነበር፡፡ ከወርቅ ውጪ ሕትመቱን የሚያቆመው የዋጋ ንረት ነው፡፡ መንግሥት ገንዘብን አትሞ ሲያሰራጭ በሕዝቡ እጅ ያለው ገንዘብ የመግዛት አቅሙ እንዲወርድ ስለሚያደርግ፣ በተዘዋዋሪ መንገድ ሕዝቡ የመንግሥትን ወጪ ሸፈነ ይባላል፡፡

ይህ የገንዘብ እጅግ በጣም አጭር ታሪክ ነው፡፡ እንግዲህ የዋጋ ንረት ማለት ባንከኞችና ፖለቲከኞች በተዘዋዋሪ መንገድ ከሕዝብ ገንዘብ መሰብሰብ ሲፈልጉ የሚያመጡት ነው፡፡ እንዴት? መንግሥትና ባንኮች በሕግ የሚያስገድድ ገንዘብ ያለቅጥ በማባዛት (በእኛ አገርና በውጩ ያለው ይለያያል ወደ ዝርዝሩ አንገባም) ገበያው ዘንድሮ ከጨመራቸው ንብረቶች በላይ የገንዘብ መጠን እንዲጨምር ሲደረግ ነው፡፡ ይህም ነባሩን ዕቃ ብዙ ገንዘብ ሲያሯሩጠው ዕቃው ላይ የሚፈሰው የገንዘብ መጠን የላቀ እንዲሆን ያስገድደዋል፡፡ እንግዲህ የዋጋ ንረት እንቆቅልሽ መልሱ የገንዘብ መጠን መብዛቱ ይሆናል፡፡

በአገራችን መንግሥትና ነጋዴዎች የአቅርቦት እጥረት እንደሌለ አረጋግጠውልናል፡፡ ስለዚህ የዋጋ ንረቱ ከአቅርቦት እጥረት እንዳልሆነ አውቀናል፡፡ በገበያ ሥርዓቱ አለመዘመንና ነጋዴዎችም ስግብግብ ሆነው ዕቃ እያከማቹ ዋጋ እንዲንር አደረጉ የሚለውን አማራጭ ማብራርያ የማልቀበልበት ምክንያት ደግሞ፣ የገበያው ያለመዘመንም ሆነ ስግብግብነቱ ዘንድሮ የመጡ አይደሉም፡፡ የዋጋ እንዲህ መናር ግን ዘንድሮ የተፈጠረ ነው፡፡

ስለዚህ ብቸኛው የቀረው ማብራርያ የገንዘብ መጠኑ ጥያቄ ነው፡፡ በግሌ የኢትዮጵያ የገንዘብ መጠን በምን ያህል እንደጨመረ፣ እንዲጨምርስ ማን እንደሚወስን፣ ወዘተ.. የማውቀው የለኝም፡፡ ሆኖም ግን በዓይኔ ባላይ እንኳ ጎል ገባ ሲባል ኳስ በየት ብታልፍ ነው? የሚለውን በግሌ መረዳት አያቅተኝም፡፡ ስለዚህም ከላይ ባስነበብኳችሁ የገንዘብ ታሪክ መሠረት የዋጋ ንረት በቀጥታ ከገንዘብ አቅርቦት መጨመር ጋር ተያያዥነት ያለው ጉዳይ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡

አሁን የዋጋ ንረቱ እንደሚቀንስ ነው የሚገምተው፡፡ መንስዔውም ከቦንድ ሽያጩ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ መንግሥት የግድቡን ግንባታ ወጪ ብር አሳትሞ ልሸፍን ቢል ኖሮ በዋጋ ንረቱ ላይ ጋዝ እንደ ማርከፍከፍ ይቆጠር ነበር፡፡ ግድቡ እየተደጎመ ያለው ግን ሕዝቡ ኪስ ውስጥ የገባውን ገንዘብ ወደ መንግሥት ካዝና በመመለስ ነው፡፡ ይህም የዋጋ ንረቱን እንዲቀዘቅዝ ያደርገዋል፡፡ በሌላ አነጋገር መንግሥት ቦንዱን ሲሸጥ በገበያ ዝውውር ውስጥ ያለውን የገንዘብ አቅርቦት እንዲቀንስ ስለሚያደርግ የዋጋ ንረቱ ይረጋጋል፡፡ በቀጣይ የገንዘብ መጠኑ እንዲህ እንዲወርድ ከተደረገ (ወይም በሌላ መንገድ እንዲጨምር ካልተደረገ) መረጋጋት ይነግሳል፡፡ ይህ ግምት የሚሠራው ግን ሌሎች ነገሮች ባሉበት ከቀጠሉ ነው፡፡ የምርት አቅርቦቱ ከቀነሰ ወይም የዓለም አቀፍ ገበያው በተለይም የነዳጅ ዋጋ የሚንር ከሆነ ሒደቱን ሊያከሽፉት ይችላሉ፡፡

ማረጋጋቱ ከዋጋ ቁጥጥር ጋር ምንም ግንኙነት አይኖረውም፡፡ ነጋዴዎቹም ስግብግብነታቸውን አይቀንሱም፡፡ የገንዘብ መጠኑ ስለሚቀንስ ብቻ ዋጋ ይረጋጋል፡፡ ይኼ ሁሉ መፋለስ የሚመጣው መንግሥታት በኢኮኖሚ ውስጥ ጣልቃ በሚገቡበት ጊዜ ነው፡፡ ይህም ማለት የአቅርቦትና የፍላጎት ሕግ የፈጠረላቸውን የከበሩ ማዕድናት መገበያያዎችን በማስወገድ፣ በሕግ የሚያስገድድ የገንዘብ ሥርዓት በማፅደቅ ለተለያዩ ወጪዎቻቸው ከሚያትሟቸው ብሮች የሚመነጭ ነው፡፡ መጀመርያውኑ በትክክል በነፃ ገበያ ሕግ ቢመራ ኖሮ አጭበርባሪው ከጨዋታ ውጪ እየሆነ ፍትሐዊ ዋጋ ይነግስ ነበር፡፡ የበለጠ ጣልቃ ገብነት ተጨማሪ ጣልቃ ገብነትን ይጋብዛል፡፡ ይህን ስል ደሞ ሊበራል ነን ባዮችን ደግፌ አይደለም፡፡  ለአገር ጠቃሚ የሆነውን እንደ መብራትና ስልክ ወይም እንደ ፀሐይ ብርሃን የሰብዓዊ መብት አካል የሆነውን ውኃ ለግል ይሰጥ የሚል ሊበራልነትን ደግፌም አይደለም፡፡ ሁሉም ሥርዓት ያስፈልገዋል፡፡ ያለ ሥርዓትና ሕግ መግባባት አይኖርም፡፡ ሆኖም ግን ሁሉም በልክ ወይም የተፈጥሮ ሕጉን ጠብቆ መሆን አለበት፡፡

ጉዳዩ እንዲህ ቀላል ከሆነ ትልልቆቹ ወይም ልሂቆቹ በዚህ ዙርያ ለምን አያስረዱንም? ለሚለው ጥያቄ መልሱ ሁሉም በሕግ የሚያስገድድ የወረቀት ገንዘብ (ፊያት መኒ) ሱስ ስለያዛቸው ነው ያስብላል፡፡ ጉዳዩን እንዳየነው ዓለም አቀፋዊም ነው፡፡ ለምሳሌ አሜሪካን ብናይ የአንድ አሜሪካዊ አማካይ ዓመታዊ ገቢ በማዕከላዊ ባንካቸው የፌዴራል ሪዘርቭ ሲስተም ሲመሠረት እ.ኤ.አ በ1913 ወደ 633 ዶላር ወይም በወርቅ ሲተመን 30.6 ኦውንስ የነበረ ሲሆን፣ ዘንድሮ ዓመታዊ አማካይ ገቢው 20,468 ዶላር ደርሷል፡፡ ይህም 3,233 ፐርሰንት አስደናቂ ዕድገት ያሳያል፡፡ ድንቅነቱ እንዲጠፋ የሚያደርገው ግን በወርቅ ሲሰላ ይህ ዕድገት 52.9 ኦውንስ ብቻ መሆኑ ነው፡፡ ይህም የ73 ፐርሰንት ብቻ ዕድገትን ያሳያል፡፡ ወረቀቱ ነው እንጂ የቆለለው እውነተኛ የመግዛት አቅም በዓመት አንድ መቶኛ ብቻ ነው የተለወጠው ይለናል  ‹‹The Creature from Jekyll  Island›› የተሰኘው እ.ኤ.አ በ1986  የታተመው መጽሐፍ፡፡

ዛሬ የአሜሪካ መንግሥት ዕዳ 14 ትሪልዮን ዶላርን አልፏል፡፡ ይህ የሱሱን አደገኛነት የሚያመለክት ሲሆን፣ የአሜሪካ መንግሥት ወጪዬን መሸፈን አልቻልኩም ብሎ ኪሳራውን የሚያውጅበትን ቀን እየቆጠረ ይገኛል፡፡ የእኛም አገር ይሁን የማንም አገር መንግሥት ደግሞ የዘመኑ ውጤት ነው እላለሁ፡፡ ስለዚህም ሁሉም ለዘመኑ ይንበረከካል፡፡ ማንም ቢመጣ ለዚህ መፍትሔ ሊያበጅለት አይችልም፡፡ በኢትዮጵያም በሕግ የሚያስገድድ የወረቀት ገንዘብ ሥራ ላይ ከዋለ ከአንድ ትውልድ በላይ ነው፡፡

ይህን አሳሳቢ ሱስ የሚገታ ምነው ጠፋ? ያላችሁ እንደሆን የችግሩን ጥንታዊነትና ዓለም አቀፋዊነት የሚያስረዳው ተደብቆ የነበረውን የማኪያቪሊያዊ ፍልስፍና ከሚያራምዱ ሰዎች ስብሰባ የተወሰደውና ከመቶ ዓመት በፊት የታተመው፡- “Protocols of the Learned Elders of Zion” የሚለውን፣ ወይም በአማርኛ ‹‹ድብቆቹ ሕገ ደንቦች›› ብዬ ተርጉሜ ለሕትመት ያበቃሁትን መጽሐፍ እንድታነቡ እጠቁማችኋለሁ፡፡

ሲጀመር እንደተናገርኩት ይህን ጽሑፍ የጻፍኩት ከእውነት መንፈስ በመነሳሳት እንጂ፣ አንበሳ አውቶብስ ላይ እንዳለው ውዝግብ ማለትም ስለኑሮ መወደድ መንግሥትን፣ ነጋዴውን፣ ጊዜውን፣ ሁሉንም ነገር ለመራገምና ለመተንፈስ አይደለም፡፡ አውቶቡሱ ላይ የሰው መውረጃ እስኪደርስ ድረስ የኑሮ ውድነቱ ጥያቄ ሳይመለስ፣ ለምን መስኮት አይከፈትም የሚለው እሰጥ አገባ አንዴ እየበረታ አንዴ እየቀዘቀዘ ከጀርባ ባጃቢነት በመደመጥ እንደሚቋጨው ወይም እንደማይቋጨው ዓይነት አታካራ ለማስነሳት ፈልጌ አይደለም፡፡ ውስጤ በመራኝና ላገኝ ከቻልኩት ሳይንሳዊ መረጃ በመመርኮዝ የደረስኩበት ድምዳሜ ይህን ይመስላል፡፡ የኑሮ ውድነቱ እንቆቅልሽ እንዲህ ይፈታል ለማለት ነው እንጂ፣ እገሌ ተሳስቷል፣ እገሌ  ደግሞ አልተሳሳተም ለማለትም አይደለም፡፡ ሁሉም የዘመኑ እስረኛ ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ይህ ጽሑፍ የፀሐፊውን አቋም ብቻ ነው የሚያንጸባርቀው፡፡ ጸሐፊውን በ seeallconcern@yahoo.com  አድራሻ ማግኘት ይቻላል፡፡

በግደይ ገብረ ኪዳን

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s