ስብሃት፡ ሃዘንተኛው ባለቅኔ

Posted: March 6, 2012 in መጣጥፍ

በግደይ ገብረኪዳን

ይህ ለማከብረው ጓደኛዬና የምርምር አጋሬ ተክሉ አስኳሉ ፌስ ቡክ ላይ ስለ ስብሃት ገ/እግዚአብሔር በፃፈው ፅሁፍ ላይ የሰጠሁት አስተያየት ሲሆን እራሱን የቻለ መጣጥፍም ሊሆን ይቸላል በማለት ልለጥፈው ወስኛለው፡፡
ተክሉ የተሰማኝን እንድነግርህ እንደምትፈልግ በመገንዘብ ስሜቴን ላጋራህ እሻለው፡፡ ስብሃት ክፉ ነገር ነው የሰበከው ላልከው አልቃወምህም፡፡ ሆኖም ግን በዚህ አስመሳይና አድር ባይ ህብረተሰብ ባጥለቀለቀው አገር ውስጥ አቋም ይዞ የተገኘ በመሆኑ እጅግ ሊደነቅ የሚገባው ሰው መሆኑ ግን ሊረሳ አይገባውም፡፡ በከንቱ አድናቂው ነን የሚሉት የሰዶም መልእክተኛ መሆኑን ቢያጤኑ ኖሮ ቀልባቸው እንደሚገፈፍ እርግጠኛ ነኝ፡፡ ሆኖም ግን የስብሃት ስህተት እኮ መርዝ ብቻ አልነበረም፡- በስህተቱ ውስጥ ትክክለኛነት ነበረበት፤ ሴሰኝነትን የመረጠው ራስ ወዳድ መሰሪ ሁኖ ሳይሆን አቅሙ የፈቀደለት እውቀት እሱ ስለሆነበት ነው፡፡ እሱ ይቅርና በመፅሃፍ ቅዱስ ውስጥም እኮ ዝሙት የሰሩ ባእድ ያመለኩ የሰው የተመኙ ለስጋዊ ፈተና የወደቁ ወዘተ. ፃድቃናት የሉም እንዴ፡፡
ደሞም ስብሃትን እኮ እንደ ሃጥያት መጀመርያ አደረከው፡፡ ከሱ በፊት ይደረጉ የነበሩ፣ ባካባቢው ያያቸውን ክስተቶች ነው የፃፈው፡፡ ስብሃት ማጨስ የጀመረው በ40 ዓመቱ መሆኑን ሰምተሃል፡፡ ስብሃት የሰራው ስህተት ከራስ ወዳድነት ሳይሆን ከየዋህነት ነው፡፡ ለዚህም አይደል መፅሃፍ ቅዱስ ብዙ ግዜ በበጎ ምግባራቸው የመፃደቁትን የሚገስፀው፡፡ በስብሃት ሃጥያት ውስጥ ፅድቅ አለበት፡፡
ሁሉም ሰው እኮ ገበሬ፣ ሁሉም አዝማሪ፣ ሁሉም ባርያ፣ ሁሉም ጌታ መሆን አይችልም፡- እነ ዳኛቸውም እነ ስብሃትም በየግላቸው ነው መገምገም ያለባቸው እንጂ ያ ለምን እንዲህ አልሆነም አይባልም፡፡ ለምን ነብር ሳር አይበላም፣ ለምን በግ ስጋ አይበላም የሚሉትን ያህል ስህተት ይሆናል፡፡
ስብሃት ደሞ ከዶስቶየቭስኪ ጋር የሚያመሳስለው እኮ እራሱም እንደተናገረው፡- አንብቦት ከመልካም ገፀ-ባህርያቶቹ፣ ፍትወት ያናወዛቸው ስላሳመኑት ነው፡- ስብሃት እነ ዲሚትሪን ነው የመረጠው…፡፡
ደሞስ እንዴት ነው ስብሃትን ከተራ ፀሃፍያን ሊነፃፀር የሚችለው እነሱ እኮ የዝሙት ጀብዳቸውን መለፈፍ የወደዱ ቁሳውያን ራስ ወዳዶች ናቸው፣ ስብሃት እኮ ስለሰው ተፈጥሮ ባህርያት መመርመር የፈለገ የምሩ ፀሃፊ ነው፡፡
በውነቱ አንዳንድ እንደነ በውቀቱ ስዩም ያሉ ፀሃፍያን ሆን ብለው ፍትወት የመረጡ ራስ ወዳዶች ናቸው፣ በኢቲቪና በየዘፈን ክሊፑ የሚታዩት ግልፍጥ ሴቶች እኮ በነጋታው ነጠላ ለብሰው ቤተ ክርስቲያን ሊሳለሙ የሚሄዱ፤ ጴንጤ ከሆኑ ደሞ ከሳምንቱ መጨረሻ ቸርች ሊደንሱ የሚሄዱ እንጭጮች ናቸው፡፡ እንዲህ ባይሆኑም ታምሪያለሽ መባልና ብር መጥባት አመላቸው ከሆኑ ጋር ማነፃፀሩ ተገቢ አይደለም፡፡
ስብሃት ባለቅኔ ነበር፡፡ በርግጥ እያረጀ ሲመጣ እየቀለለ ሳይመጣ አልቀረም፡፡ አንበሳ እንኳ ሲያረጅ የዝንብ መጫወቻ ይሆናል አይደል የሚባለው፡፡ ግን መንፈሱ ቀና ነበረች፡፡ አንድ የኬርኬጋርድን ጥቅስ ላስታውስህ፡
“ባለቅኔ ምንድን ነው?ሃዘንተኛ የሆነ ሰው በልቡ ጥልቅ ስቃይ አምቆ የያዘ በከናፍርቱ ግን ቃላት ሲያልፉ ጥኡም ዘፈንን ይመስላሉ፡፡” ይላል፡፡ ይህን አይነት ሰው ከአንዲት ከርታታ ጋር ማነፃፀር አይገባም፡፡
ስብሃት በውስጡ ጥልቅ ስቃይ የሸሸገ ባለቅኔ ይመስለኛል፡፡ እናም ከዚህ ቀና መንፈሱ አንፃር እንገምግመው፡፡ እንጂ ወጣቱን አበላሸ ብለን አንፍረድበት፡፡ ወጣቱም እኮ የመምረጥ መብት አለው፡፡ ቀናነት የሌለው ወጣት ከስብሃት መጥፎ ነገር ብቻ ይታየዋል፡፡ በዚሁ ከቀጠልኩ መቋጫ አይኖረውም፣ ሰውየውን ግን በዚህ መልኩ እንረዳው፡፡

ተክሉ ዛሬ ኮምፒውተር በሚያስፈልገኝ ቀን አጥቼ ዋልኩኝ ሆኖም ግን እንደምንም የምለውን ለማለት ተሟሙቻለው፡፡ እርግጥ ነው ሰዎች በተለያየ መንገድ ተፅእኖ ይፈጥራሉ፣ የስብሃት ጎጂ ተፅእኖንም አልካድኩም፡፡ ማለት የፈለኩት ግንበዚህ ጎጂ ተፅእኖ በመፍጠሩ ምክንያት እንደ ስብሃት አይነቱ የስነ ፅሁፍሰው ሊወገዝ አይገባውም ምክንያቱም ስብሃት እንደ ኪንሰይ ሳይንቲስት ነኝ እንደማርክስ ፈላስፋ ነኝ (ሕብረተሰብ ቀራጭ) አልወጣውም፡፡ እሱ ባለ ቀኔ ነው፣ የሰው ባህርያት የሰው እጣፈንታ እና ተፈጥሮ ነው የሚመስጡት፡፡ የቅኔ መንፈስ ደሞ የምትረካው የግድ የተሰማውን ሲተነፍስ ነው፡፡ እንጂ እሱ ተከተሉኝ እኔ ነኝ ልክ አላለም፡፡ ሂወትን እንዲህ አየኋት፣ ገረመቺኝ ነው ያለው፡፡ ሌላ ሰው ማጥፋት ሲያምረው በሱ ማሳበብ ያሳብባል፡፡
እና ይህ የነብሱን ስቃይ ሲተነፍስ ወህኒ ስለማያስወርድ አቋም አልለውም ማለት አንችልም፡፡ መንግስት ብቻ አይደለም የሚፈራው እኮ፣ እሱ እማ ማንም ሂወት የመረረው ከመንግስት ጋር ሊሳፈጥ ይችላል፣ ስብሃት እኮ ከዘላለማዊው ሃያል ጋር ነው ሲሳፈጥ የኖረው፡፡ (መደገፌ ሳይሆንምን ያህል ጥንካሬ እንደሚጠይቅ ለማስታወስ ነው፡፡)
ዝሙት ፈፀመ ብለህ አትውቀሰው እኮ አላልኩም፡፡ ግን ያየውን ለምን ይፅፋል ማለት አይቻልም ነው ያልኩት፣ ባለ ቅኔ ነውና፡፡
እርግጥ ነው በሂወቱ መጨረሻ ሳይጃጃል አልቀረም፣ ሆኖም ግን እኔ የተከራከርኩለት ይህ ደራሲ ህሊና ያለው እና ለደረሰባቸው እውነቶች የቆመ ነው፡፡ ግዝያዊ ጥቅም መርጦ ሂወቱን በከንቱ በሹፈት ማሳለፍ የፈለገ ተራ ሰው አይደለም ለማለት ብዬ ነው፡፡
ሰቃይ በውስጡ ስለመያዙ መጀመርያውኑ ባለቅኔ የመሆኑ ሚስጥር ነው፡፡
በመጨረሻም ደግሜ የማስታውስህ ስብሃት አይነኬ ነው አትውቀሰው ለማለት ፈልጌ ሳይሆን እሱን የምናይበት መነፅር ይለያል ነው፡፡ የዘነጋሁት ካለ እጨምራለው ዛሬ ኮምፒትር ጉድ አርጎኛል፡፡

Wednesday at 08:25 ·

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s